ለዓለም ዋንጫ ደ.አፍሪካ ለመሄድ 50 ሺህ ብር የከፈሉ ታገዱ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሰኔ 9 ቀን 2002 ዓ.ም. June 16, 2010)፦ በደቡብ አፍሪካ የሚካሄደውን የ19ኛውን የዓለም ዋንጫ ውድድሮች ለማየት ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ 50 ሺህ ብር የከፈሉ 550 ሰዎች ፈቃድ ተከለከሉ። ያስያዙት ገንዘብ አልተመለሰላቸውም።
ፊፋ ለዓለም ሀገራት በየደረጃው የተመልካች ኮታ የሰጠ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ250 ሰዎች ዕድል መስጠቱ ታውቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስፈርቶችን በማዘጋጀት የዓለም ዋንጫን ለማየት ወደ ደቡብ አፍሪካ መጓዝ ለሚፈልጉ ሰዎች ፌዴሬሽኑ ያወጣውን መመዘኛ ካሟሉ መሄድ እንደሚችሉ ይገልፃል። ይህንኑ ተከትሉ በርካታ ሰዎች የተጠየቀውን 50 ሺህ ብር በመክፈል ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ተመዝግበዋል።
ፌዴሬሽኑ ከ650 በላይ ሰዎችን ከመዘገበ በኋላ፣ ውድድሩ ሊጀመር ሦስት ቀን ሲቀረው ከተመዘገቡት ውስጥ ለ100 ሰዎች ብቻ በመፍቀድ ቀሪዎቹን ግን ሳይቀበላቸው ቀርቷል። ፌዴሬሽኑ ያልተቀበለበትን ምክንያትም በግልጽ ለተመዝጋቢዎቹ አለመግለጹን ለመረዳት ችለናል። ከዚህም ሌላ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ፤ ያልተፈቀደላቸው ሰዎች ያስያዙት ገንዘብ ሳይመለስላቸው ቀርቷል።
ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን እንደገለጹት ከሆነ ከተመዘገቡት 650 ሰዎች ውስጥ ዕድሉን አግኝተዋል የተባሉትና 100 ሰዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዙት የዓለም ዋንጫን ለመመልከት ሳይሆን፤ ለስደት የሚጓዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ጉዳዩ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ጥርጣሬ ስላሳደረበት የሰዎቹን ቁጥር ፌዴሬሽኑ ለመቀነስ መገደዱን ምንጮቻችን ሳይጠቁሙ አላለፉም።