ፊፋ ኢትዮጵያን ከሁሉም ውድድሮች አገዳት
ምክንያቱ የዶ/ር አሸብር ከኢ.እ.ኳ.ፌ. ፕሬዝዳንትነት መባረር ነው
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. July 30, 2008)፦ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ከማናቸውም ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንዲሁም ከሌሎች ሀገሮች የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ጋር የሚኖረውን ግንኙት ከትናንት ጀምሮ ማገዱን አስታወቀ። መንስኤው የዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትነት መባረር ነው።
የፊፋ እገዳ ኢትዮጵያን እ.ኤ.አ. 2010 ለሚደረገው የዓለም እግር ኳስ ማጣሪያ እንዲሁም ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በቅርቡ ሞሮኮ ላይ ከነኀሴ 30 - ጳጉሜን 2 ቀን 2000 ዓ.ም. (September 5 – 7 2008) እንዳትሳተፍ ያደርጋታል።
ፊፋ እገዳውን የጣለበት ምክንያት የካቲት 2000 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (ፊፋ) እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እውቅና ያላቸውን የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስን አባርሮ በምትካቸው አቶ አሕመድ ያሲንን በመሾሙ ነው።
የየካቲቱን ጠቅላላ ጉባዔና ውሳኔውን ፊፋ ያልተቀበለውና እውቅና ያልሰጠው ስለነበር፤ ሁለቱንም ወገኖች አግኝቶ አስታራቂ ሃሳብ ለማቅረብ ጥረት አድርጎ ነበር።
ፊፋ እና ካፍ በጋራ በመሆን መጋቢት ወር ላይ ሮድ ማፕ አዘጋጅተው ለጉዳዩ መፍትሔ ለመሻት ሞክረዋል። በዚህ ባዘጋጁት የመፍትሔ ሃሳብ ላይ ፊፋም ሆነ ካፍ እውቅና የሚሰጡት ለዶ/ር አሸብር መሆኑን ገልጸው፤ መጋቢት 20 ቀን 2000 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ እንዲካሄድ ብለው ነበር።
የዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ከፕሬዝዳንትነት መባረር ፊፋ እና ካፍ የሚቀበሉት መጋቢት 20 እንዲደረግ አቅደውት በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተሳታፊዎች በሚሰጡት ምስጢራዊ ድምፅ ሁለት ሦስተኛው (2/3) ከደገፈው ብቻ እንደሚሆን ባወጡት ሮድ ማፕ ገልፀው ነበር። ነገር ግን የታቀደው ጠ/ጉባዔ ሳይካሄድ ቀርቷል።
ከዚህም ሌላ ዶ/ር አሸብር ወደ ቢሯቸው እንዳይገቡና የተደረጉ ከመሆኑም በላይ በሮድ ማፑ ፊፋ እና ካፍ ያሰፈሩት አንዱ አስታራቂና የመፍትሔ ሃሳብ ተፈፃሚነት አለማግኘቱን ፊፋ ገልጿል።
ፊፋ አክሎም ሮድ ማፑ ተፈፃሚ ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ገልጾ፣ እገዳውን መጣሉን አስታውቋል።