የቦንብ ፍንዳታዎቹ ዝርዝር ዘገባ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 7 ቀን 2000 ዓ.ም. April 15, 2008)፦ ትናንት በሁለት የኖክ የነዳጅ ማደያዎች የደረሰውን ፍንዳታ የአሸባሪዎች ጥቃት ነው ሲል የኢህአዴግ መንግሥት ገለጠ። ድርጊቱን አቶ አየለ ጫሚሶ እና አቶ ልደቱ አያሌው ማውገዛቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ገለጡ።
ትናንት ማምሻውን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ወደ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ገርጂ ኢምፔሪያል ሆቴል አካባቢ እና መገናኛ ለም ሆቴል አካባቢ ነጭ ጋዝ ለመግዛት የተሰለፉ ሰዎች ላይ ነበር ቦንቦቹ በተመሳሳይ ሰዓት የፈነዱት።
ፍንዳታው እንደተከሰተ ሁለቱም አካባቢዎች በፌዴራል ፖሊሶችና የመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች አካባቢውን ጠርቅመው ዘግተው ሰዎች አደጋው ወደተከሰተበት ስፍራ እንዳያልፉ ይከለክሉ እንደነበር የአካባቢውን ሰዎች ያነጋገረው የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ዘገባ ያስረዳል።
የመንግሥት የደኅንነት ኃይሎች እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ፍንዳታው የደረሰባቸውን ነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ዘግተው አካባቢው ከፍተኛ ውጥረት ይታይበት የነበረ ሲሆን፣ በተለይ በአዲስ አበባ ጥበቃው ከሌላው ጊዜው የተለየ እንደነበር ታውቋል።
በፍንዳታው ምክንያት ገርጂ 2 ሰዎች ሲሞቱ፣ አንድ ሰው ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲደርስበት፣ 8 ሰዎች ደግሞ መለስተኛ የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው እና በለም ሆቴል አካባቢ በሚገኘው የነዳጅ ማደያ ደግሞ አንድ ሰው ሲሞት፣ ሁለት ሰዎች እንደቆሰሉ ለማወቅ ተችሏል።
ሕይወታቸውን ያጡትንና የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች የዕድሜና የጾታ ሁኔታ ጨምሮ በንብረት ላይ የደረሰውን አደጋ ኦፊሴሊያዊ ማረጋገጫ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ለጊዜው አልተገኘም። ኢትዮጵያ ዛሬ ለማጣራት ያደረገው ሙከራ አልተሳካለትም።
የኢህአዴግ መንግሥት ፍንዳታውን አስመልክቶ "የአሸባሪዎች ጥቃት ነው" ሲል የተደመጠ ሲሆን፣ ድርጊቱንም የሚያወግዝ መግለጫ ማውጣቱ ታውቋል። ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት እስከዛሬ ማምሻው ድረስ ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን ግን የለም።
ከዚህም ሌላ ምርጫ ቦርድ የ"ቅንጅት"ን ሕጋዊ እውቅና የሰጠው ድርጅት መሪ የሆኑት አቶ አየለ ጫሚሶ እና የኢዴአፓ-መድኅን ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ጥቃቱን ማውገዛቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኀን እንደዘገቡት ዘጋቢያችን ማምሻውን ካስተላለፈልን ዘገባ ለመረዳት ችለናል።
ኖክ (ናሽናል ኦይል ኩባንያ) የተቋቋመው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ንብረትነቱ የሦስት ባለሀብቶች መሆኑ ታውቋል። የአንበሣውን ድርሻ የያዙት ሼክ መሐመድ ሁሴን አላሙዲንን ሲሆኑ 75 በመቶ አክሲዮን ሲኖራቸው፣ 15 በመቶ አቶ አብነት ገ/መስቀል እና ቀሪውን 15 በመቶ አቶ ታደሰ ጥላሁን የተባሉ አንድ ሌላ ባለሀብት ንብረት መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
ኖክ በሀገሪቱ 150 የነዳጅ ማደያዎች እንዳሉት ይነገራል። በፍንዳታው ከተጎዱት ውስጥ የኢምፔሪያል ሆቴሉ ቀድሞ ቶታል ይባል የነበረው ሲሆን፣ ኖክ ከተቋቋመ ወዲህ ከቀድሞ ባለቤቱ ላይ ገዝቶት ንብረቱ ያደረገው መሆኑ ታውቋል። ለም ሆቴል አጠገብ ያለውን ግን ኖክ ራሱ ያስገነባው እንደሆነ የደረሰን ዘገባ ያስረዳል።
ኖክ ከተቋቋመ ከተመሠረተ ወዲህ የከፈታቸውን የነዳጅ ማደያዎች ከሌሎች ግለሰቦችና ኩባንያዎች በመግዛት እንዲሁም ቀሪዎቹን ራሱ ኩባንያው የገነባቸው ናቸው።
በተያያዘ ዘገባ የጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ እንደሆኑ የሚነገርላቸውና የጠ/ሚ/ሩ ልዩ አማካሪ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን ለሮይተርስ አደጋውን የፈፀሙት በኤርትራው መንግሥት የሚደገፉትና የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙት ኦነግ (የኦሮሞ ነፃነት ግንባር) እና ኦብነግ (የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር) ናቸው ሲሉ ወንጅለዋል።
ሮይተርስ የኦብነግ ቃል አቀባይ የሆኑትን አቶ አብዲራሐም መሐዲን በስልክ ከሚገኙበት ከሎንዶን አነጋግሯቸው "በዚህ ጥቃት የኦብነግ እጅ በፍፁም የለበትም። ጥቃቱ የተፈፀመው እኛ ከምንንቀሳቀስበት እጅግ ርቃ በምትገኘው አዲስ አበባ ነው የተፈፀመው። ከዚህም በተጨማሪ ንፁኀን (ሲቪል) ዜጎችን የመጉዳት ፖሊሲ አንከተልም" ሲሉ ድርጊቱን ድርጅታቸው እንዳልፈፀመና ኃላፊነቱን እንደማይወስድ ገልጠዋል።