በአካባቢው የጎሣ ችግር እንዳይከሰት ተሰግቷል

ልዩ ሪፖርታዥ

Debre Libanos MonasteryEthiopia Zare (ማክሰኞ ጥር 27 ቀን 2000 ዓ.ም. February 5,2008):- ለ838 ዓመታት በታሪካዊ ገዳምነት የሚታወቀው የደብረ ሊባኖስ ገዳም አካባቢ ወደ ቀበሌነት መለወጥን የተቃወሙ መነኮሳት፤ የገዳሙ ወደ ቀበሌነት መለወጥ የኃይማኖታዊ ተግባሩ ጋር በፍጹም የሚቃረን ነው ሲሉ አቤቱታቸውን ለማሰማት ወደ ፓትሪያርኩ ቢሮ መምጣታቸውንና በእንግልት ላይ መሆናቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ። ከአዲስ አበባ የደረሰን ሪፖርት እንዲህ ተዘግቧል፦

ጥር 23 ቀን 2000 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ በርካታ መነኮሳት ከደብረሊባኖስ ገዳም መምጣታቸውን ሰምተን ወደዛው አመራን።  መግቢያው በር ላይ ባሉ ፌደራል ፖሊሶች ከፍተኛ ፍተሻ ተደርጎልን የምንገባበትን ቦታ ዋሽተን ወደ ውስጥ ዘለቅን።

ጠ/ቤተ ክህነት ምንም እንኳን ቢሮ ቢሆንም ፓትሪያርኩን ጨምሮ የኃይማኖት አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች የሚገኙበት ቦታ እንደመሆኑ መንፈሣዊነትና የጸጥታ ድባብ የነገሰበት ይሆናል ብለን ጠብቀን ነበር። ነገር ግን በር ላይ ካጋጠመን የቤተ መንግሥት መግቢያ አይነት ፍተሻ አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ የደህንነት ሠራተኞች ዓይኖች ተከተሉን። ይሄኔ ወደ ተሰበሰቡት መነኮሳት ከመሄድ ይልቅ ቆም አልንና ዙሪያ ገባውን መቃኘት ጀመርን። 

የጎሣዬ ዘፈን ጮክ ብሎ ይሰማል ምናልባት ከአጥሩ ውጭ ሊሆን ይችላል ብለን በማሰብ ዙሪያ ገባውን ማተርን። አንድ የፌደራል ፖሊስ በተቀመጠበት ወንበር ላይ ተንፈራጦ አግሩ ላይ መሳሪያውን አጋድሞ ድምጹን ጨምሮ የከፈተውን ሙዚቃ ያዳምጣል። 

ከሄድንበት ጉዳይ ይልቅ ለምን በዚህ እንደተመሰጥን ከጓደኛዬ ጋር ተነጋገርን "ከፌደራል ፖሊሱ ጥበቃ የዘፈኑ" አለኝ። "ምናልባት ቦታውን እንደኃይማኖት ቦታ ጠብቀነው ይሆን?" የሚል ምላሽ ሰጠሁት። ጠ/ቤተክህነት ቢሆንስ "ፓትሪያርኩን ጨምሮ የኃይማኖት አባቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ያሉበት እኮ ነው" የሚል ምላሽ ሰጠኝ። "በል ወደመጣንበት እንመለስ" ስል ወደመነኮሳቱ አመራን። 

ለሊቱን ሲጓዙ አድረው ሲነጋጋ አዲስ አበባ የገቡት መነኮሳት 60 ናቸው። ሁሉም በየጥጋ ጥጉ ቆመው ወደ ፓትርያኩ ግቡ እስኪባሉ ይጠብቃሉ። የመጣንበትን በማንሾካሾክ ተናግረን ሸሸግ ማያ ጓሮ ነገር ፈልገን ከተወሰኑት ጋር ተነጋገርን። ምክንያታቸውንም ጠየቅናቸው። 

"ደብረ ሊባኖስ ገዳም 838 ዘመን ታሪክ ያለው ትልቅ ኃይማኖታዊ ቦታ ነው። ገዳሙ በወንዞች መኃል ጎድጓዳ ቦታ ላይ የሚገኝ ቅርስ ሊሆን የሚችል ሀብት ነው" አሉን። 

ከዚሁ ገዳም ጋር በተያያዘ የጸበል ቦታ ለመጠቀም ለሚመጡ ምዕመናን ማረፊያ እንዳይቸግር በማለት ገዳሙ ከ1 ብር እስከ 10 ብር የሚከራዩ 500 የሚሆኑ ቤቶችን ሰርቷል። 

እንደ መነኮሳቱ ገለጻ ለጸበል መጥተው እነዚህን ቤቶች በመከራየት ከተጠመቁ በኋላ ወደ ከተማ መመለስ እንደማይፈልጉ በመናገር እዛው ገዳሙን በመጠጋት መኖር የጀመሩ በርካቶች ናቸው። 

ከጊዜ ብዛት ግን እነዚህ ነዋሪዎች አካባቢው በኦሮሚያ ክልል ስር እንደመሆኑ እንደ ቀበሌ እንዲዋቀር ይጠይቃሉ። ገዳሙ በበኩሉ የቦታው ባለቤትነት የገዳሙ በመሆኑ፣ ታሪካዊ የኃይማኖት ቦታ በመሆኑ፣ እንደ ቀበሌ ከተዋቀረ የኃይማኖት ቦታ መሆኑ ይቀርና ዓለማዊ ቦታ ይሆናል። በገዳሙ ውስጥ የቆሎ ተማሪዎች፣ ሴቶች መነኮሳት፣ ወንዶች መነኮሳት፣ መምህራኖች፣ ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ጥለው የመጡና የመነኑ ወደ አምስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ያሉበት ቦታ በመሆኑ በምንም ነገር ሊረበሽ የማይገባው ኃይማኖታዊ ቦታ ስለሆነ ለማንም ሊሰጥ አይገባም ሲሉ ተቃውሞ ያስነሳሉ። 

ጉዳዩ ወደ ዞን አስተዳዳሪዎች ከዛም ወደ ክልሉ ይደርሳል። እንደ መነኮሳቱ ገለጻ ከሆነ ምንም መፍትሄ አልተገኘም። እንደውም መነኮሳቱ ድብደባና ተኩስ ይፈጸምባቸዋል። ከዛም አልፎ ወደ አጥር ዳር ያሉ ቤቶችን ያፈራርሱባቸዋል። ገዳሙ ተጠሪነቱ ለእጨጌ ዘመንበረ ተክለኃይማኖት ፓትሪያርኩ በመሆኑ ከሦስት ጊዜ በላይ ለሳቸው ያመለክታሉ። 

ችግሩ እንደሚፈታ ተነግሮአቸው እንዲመለሱ ይደረጋል። ግን ተመልሰው ሲሄዱ ድብደባው እንደሚቀጥልባቸው ይናገራሉ። "ምን ታመጣላችሁ?" ይባላሉ። 

ይህንን የሚፈጽሙት ደግሞ ሁሉም አይደሉም ይላሉ። የተወሰኑት የገዳሙን ሕግ አክብረው ለመጡበት ዓላማ የተሰለፉ ናቸው ይላሉ። 

"መነኮሳት ዓለም በቃን ብለው ገዳም ከገቡ በኋላ እንዴት እንዲህ አይነት ነገር ገዳም ድረስ ተመጥቶ ይፈጸምባቸዋል?" ሲሉም ይጠይቃሉ። "ለፓትሪያርኩ ስናመለክት ተነጋግረው ከመፍታት ይልቅ እዛው ጠብቁ በማለት መነኮሳቱን ሊያስጨርሱ ነው" ሲሉ ፓትሪያርኩን ይወቅሳሉ።

"መንግሥትም ቢሆን በሌላ ቦታ ሕገ-ወጦችን እንደሚያስነሳው ሁሉ እዛም ማስነሳት ወይም በሰላም የጠበል ቦታው እንዲከበር ማድረግ ሲችል ዝም ብሎ አንድ ዓመት ሙሉ የሚያየው ሊያስጨርሰን ነው" ሲሉ አቤቱታ ያሰማሉ። 

ችግሩ በቀላሉ ይፈታል በሚል ሲጠብቁም ከፍተኛ የሆነ ድብደባ እየደረሰባቸው በመሆኑ በአፋጣኝ ምላሽ ካላገኙ አካባቢውን ጥለው ወደ ሌላ ቦታ እንደሚሰደዱ የመጨረሻ መልዕክታቸውን ለመንገር ወደ ፓትሪያርኩ መምጣታቸውን ገልጸውልናል። ፓትርያርኩም መጥተው ለጥቂት ጊዜ ካነጋገሯቸው በኋላ "ከሚመለከተው አካል ጋር ተነጋግሬ ምላሽ እሰጣችኃለሁ" ካሏቸው በኋላ የሚመገቡትና የሚጠለሉበት የሌላቸውን መነኮሳት ትተዋቸው መሄዳቸውን ተረዳን። ይህ ከሆነ በሀኋላ ነበር የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ውስጥ አንዳንድ የመነኮሳቱን ስቃይና እንግልት የተመለከቱ ምዕመናንና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ምግብና ልብስ በማምጣት መነኮሳቱን ከረሃብና ከእርዛት የታደጓቸው።

ይህንን የምዕመናኑን ጥረትና እንክብካቤ ሁኔታ የሰሙት አቡነ ጳውሎስም ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ወደ መነኮሳቱ ተመልሰው በመምጣት ጉዳዩን የሚመለከተው መንግሥት ስለሆነ ተነጋግሬ ውጤቱን እነግራችኋለሁ ብለው እንደተለዩዋቸው ለማወቅ ችለናል።

የአቡነ ጳውሎስን ድርጊት የተከታተሉ የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንት እንደሚሉት የዚህን ታላቅ ገዳም ችግር ራሳቸው ፓትሪያርኩ ሊፈቱት ሲገባ ከመንግሥት ጋር በማገናኘት ከማለፍ ይልቅ ለችግሩ ፈጣን እልባት መስጠት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል። መንግሥትና ፓትሪያርኩ 838 ዓመት ተባብረው የኖሩትን የገዳሙን መነኮሳት እና የአካባቢውን ነዋሪዎች ቀላል ችግር ወደ ጎሣ ግጭት እንዲያመራ በር እየከፈቱ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።     

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!