ቴዲ አፍሮ ዛሬ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ገባ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. April 16, 2008)፦ ዝነኛው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከዚህ ቀደም "በመኪና ሰው ገለህ አምልጠሀል" በሚል ተከሶበት በነበረው ክስ ምክንያት የፌደራል ዓቃቢ ሕግ የዋስትና መብት ሊሰጠው አይገባም በማለቱ የዋስ መብቱን በሚመለከት ውሳኔ እስኪሰጥ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት የተላከ መሆኑን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።
በዛሬው ዕለት በቴዲ ላይ የቀረበበት ክስ ያለመንጃ ፍቃድ በመንዳት እና ሆን ብሎ ሰው ገድሎ በማምለጥ ክስ ነው። ጠበቃው አቶ ሚሊዮን አሰፋ "ደንበኛዬ ቴዎድሮስ ካሳሁን ድርጊቱን ካለመፈጸማቸውም በላይ ክሱ ሊቀየር ይገባዋል" ሲሉ የተከራከሩ ሲሆን፣ ዳኛ ልዑል ገ/ማሪያም የፌዴራል ዓቃቢ ሕግ እና ጠበቃው ያቀረቡትን ክርክር ካዩ በኋላ ውሳኔ ለመስጠት ለመጭው ሰኞ ቀጠሮ በመስጠት ተከሳሽ ቴዎድሮስ ካሳሁን ቀጠሮው እስኪደርስ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት እንዲቆይ የተወሰነ መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ ለአራት ሰዓታት ያህል ፍርድ ቤቱ አካባቢ በሚገኘው ማቆያ እስር ቤት በእስር ከቆየ በኋላ ወደ ቃሊቲ መውረዱን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ዳኛው አቶ ልዑል ገ/ማሪያም የቅንጅት መሪዎችን ክስ ካዩት ዳኞች መካከል የቀኝ ዳኛ ሆነው ተሰይመው የነበሩ ሲሆን፣ በአስቸጋሪነታቸው የሚታወቁ ከመሆኑም በላይ፤ ዛሬ በቴዲ አፍሮ ላይ የቀረበበትን ክስ የዋስትና ውሳኔ ዛሬውኑ መወሰን ይችሉ እንደነበር ታዛቢዎች ይናገራሉ።