የቴዲ አፍሮ ክስና እስር ዝርዝር ዘገባ

  • ‘ቃሊቲ’ መውረዱ ሴት አድናቂዎቹን በእንባ አራጨ

Teddi Afro

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 10 ቀን 2000 ዓ.ም. April 18, 2008)፦ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ሚያዝያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል ችሎት፤ (ለሁለት ዓመታት የዘለቀውንና የቅንጅት አመራሮች .. የተከሰሱበትን የሁለተኛ ወንጀል ችሎት በቀኝ ዳኝነት ሲያስችሉ በነበሩት) ዳኛ አቶ ልዑል ገብረ ማርያም ተሰይሟል።

 

Teddi Afro

ከጠዋቱ 3 ሰዓት ከ30 ደቂቃ የተሰየመው ይኸው ችሎት ከጠዋቱ 5 ሰዓት አካባቢ ሲሆን በወንጀል መዝገብ ቁጥር 06226 የተከሰሰው ተከሳሽ እንዲቀርብ ተጠራ።

 

ችሎቱ መደበኛ በመሆኑና በዕለቱ በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው የታዋቂው ዘፋኝ የአርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን መዝገብ መሆኑን በችሎት ታዳሚው የሚታወቅ ባለመሆኑ፤ ቴዲ አፍሮ ከጠበቃው ጋር ወደ ተከሳሽ ሳጥን ገብቶ ሲቆም የችሎት ተከታታይ ዓይን ወደ ሣጥኑ ተወረወረ።

 

ዳኛው፤ መዝገቡ በችሎት ተከፍቶ ሊቀርብ የቻለበትን ምክንያት ማሰማት ጀመሩ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በቴዎድሮስ ካሳሁን ያቀረበው ክስ “መጠጥ ጠጥቶ ካለመንጃ ፈቃድ በማሸከርከር ሰው ገጭቶ ከገደለ በኋላ ምንም እርዳታ ሳያደርግ አምልጧል” የሚል ነው። ዓቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሰው አንቀጽ በ1997 ዓ.ም. በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ፤ በቸልተኝነት ሰው መግደል የሚለውን አንቀጽ 543 ንዑስ ቁጥር 3 መተላለፍ የሚል ነው።

 

ቴዲ አፍሮ ተላልፎታል ተብሎ የተጠቀሰበት ንዑስ ቁጥር 3 “ጥፋተኛው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የገደለ ወይም ወንጀሉን የፈጸመው ግልጽ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያ ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ እራሱን ከኃላፊነት ነፃ በሚያወጣ ሁኔታ ውስጥ ካስገባ በኋላ ቢሆንም እንኳ፣ ቅጣቱ ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት ለመድረስ የሚችል ጽኑ እስራትና ከብር አሥር ሺህ እስከ አሥራ አምስት ሺህ የሚደርስ መቀጮ ይሆናል” ይላል።

 

የቴዲ አፍሮ ጠበቃ አቶ ሚሊዮን አሰፋ ደንበኛቸው ቴዎድሮስ ካሳሁን በዋስ እንዲፈታና ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ያቀረቡት አቤቱታ በዓቃቤ ሕግ ተቃውሞ ገጥሞታል። ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ “ተከሳሹ ቴዲ አፍሮ ሆን ብሎ ሰው ገጭቶ በማምለጥ የተከሰሰ በመሆኑ በዋስትና ሊለቀቅ አይገባውም” ሲል ተከራክሯል።

 

ጠበቃው አቶ ሚሊዮን ደንበኛቸው አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን “ድርጊቱን አልፈጸምኩም” ማለቱን በመግለጽ በዋስ እንዲለቀቅ ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከአዳመጠ በኋላ ለተከሳሹ ቴዲ አፍሮ የዋስትና መብት ይፈቀድለት አሊያም ይከልከል የሚለውን ለመወሰን ለሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2000 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

 

የክሱ አመጣጥና ሂደት

ቴዲ አፍሮ ረቡዕ ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. ጠዋት ከካናዳ ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል። ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. በሲ.ኤም.ሲ. ይኖርበት ከነበረው መኖሪያ ቤቱ “ሰው ገጭተህ አምልጠሃል” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ሜክሲኮ በሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ነክ ፍርድ ቤት የሰባት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆበት ወደ ታሰረበት ጣቢያ ይመለሳል።

 

ቅዳሜ ጥቅምት 25 ቀን 1999 ዓ.ም. ከታሰረበት ጣቢያ የ50 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ይለቀቃል። በቀጠሮው መሠረትም ፍርድ ቤት ሲቀርብ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሚመለከተው አካል ያስተላለፈ በመሆኑ የቀጠሮ መዝገቡ እንዲዘጋለት ጠይቆ መዝገቡ ተዘግቷል።

 

ጉዳዩን የያዘው ፖሊስም ኅዳር 7 ቀን 1999 ዓ.ም. በፖሊስ መዝገብ ቁጥር 2749/99 ቁጥር 8206/ወ/መ18 በተጻፈ መሸኛ ደብዳቤ “ቴዎድሮስ ካሣሁን ገርማሞ ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ከአስር ደቂቃ ሲሆን በአራዳ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 17 ክልል በቤተ መንግሥት አካባቢ ንብረትነቱ የግላቸው በሆነው ኮድ 2-59868 አዲስ አበባ BMW አውቶሞቢል መኪናቸው ደጉ ይበልጣል የተባለ እግረኛ ገጭተው ገድለው ካመለጡ በኋላ፣ በፍለጋ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ የተደረገባቸው ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት የምርመራ መዝገቡ ተጠናቆ ከዚህ ሸኚ ደብዳቤ ጋር ተልኳል።” የሚል ደብዳቤ ጽፎና ምርመራውን ማጠናቀቁን ገልጾ መዝገቡን ለአዲስ አበባ ፍትህ ሚኒስቴር ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስተላለፈ።

 

ስለ ሟች “ፎርቹን” ጋዜጣ አውጥቶት የነበረው የሕይወት ታሪክ

ቴዲ አፍሮ በመኪና ገጭቶ ገድሎታል በሚል የተጠረጠረበትን የሟች ደጉ ይበልጣል የሕይወት ታሪክ “ፎርቹን” የተባለ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ የሟች አባት አቶ ታምሩ ተፈሪን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሟች ከጎጃም መጥቶ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ከአጎቱ ጋር ይኖር የነበረ የ18 ዓመት ወጣት ነው። ደጉ መጠጥ ከሚጠጡ ልጆች ጋር በመግጠሙ ቤቱን ጥሎ ለጎዳና ሕይወት ይዳረጋል። ነገር ግን በሣምንት አንዴ ወይም ሁለቴ ወደ ቤተሰቦቹ በመምጣት ይጠይቃቸው እንደነበር ነው።

 

ዓርብ ጥቅምት 24 ቀን 1999 ዓ.ም. ደጉ በመኪና አደጋ መሞቱ ተነግሯቸው አስከሬኑን ከምኒልክ ሆስፒታል ወስደው በእንጦጦ ቁስቋም ማርያም ቤተክርስቲያን መቅበራቸውን ጋዜጣው ዘግቦ ነበር።

 

ቴዲ በወቅቱ ለአዲስ አድማስና ሪፖርተር ጋዜጣ የሰጠው መልስ

“ሰውን የሚያህል ክቡር ነገር ገጭቼ ላመልጥ አልችልም፣ እኔ ድርጊቱ ተፈጸመ በተባለበት ቦታ አልነበርኩም፣ 'ሰው ገጭቶ አምልጧል' የተባለው ወሬ ሐሰትና ጉዳዩም ክብሬን የሚነካ ነው” ነበር ያለው።

 


የቴዲ አፍሮ የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ ከተዘጋ ከአንድ ዓመት ከአምስት ወር በኋላ ክስ ተመስርቶበትና በዋስ የመለቀቅ መብቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቶ ቃሊቲ ወደሚገኘው ማረሚያ ቤት ወርዷል። ፍርድ ቤቱ ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን ሲሰየም፣ የዋስትና መብቱን ይፈቅድለታል አሊያም ይከለክለዋል።


ዓቃቤ ሕግ በመሰረተበት ክስና በጠቀሰበት አንቀጽ ግን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ከአምስት እስከ አስር ዓመት ሊደርስ በሚችል ጽኑ እስራትና ከብር አስር እስከ አሥራ አምስት ሺህ ብር ሊቀጣ ይችላል።

 

ቴዲ አፍሮ ፍርድ ቤቱ በዋስትና ጥያቄው ላይ ውሳኔው እስከሚሰጥበት ሰኞ ድረስ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቆይ ከዳኛው ትዕዛዝ ሲሰጥ ቴዲ አፍሮ ምንም ቃል ሳይተነፍስ ችሎቱን ለቆ ወጥቷል።

 

ትዕዛዙ የደረሳቸው ፖሊሶች ወደ ማረሚያ ቤት በሚወስዱበት መኪና ውስጥ አብረዋቸው የሚጓዙት ሌሎች እስረኞች ጉዳያቸው እስኪጠናቀቅ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ በሚገኘው የቆርቆሮ ማረፊያ ውስጥ ቴዲ አፍሮን አስቀመጡት።

 

በወቅቱ አብዛኛው የፍርድ ቤቱ ሠራተኛ፣ ለጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት የመጡና የቴዲን መታሰር የሰሙ አድናቂዎቹ ፍርድ ቤቱን ለማጨናነቅ ችለዋል። ቃሊቲ ሊወርድ መሆኑን የሰሙ ሴቶችም እንባቸውን አፍሰውለታል። ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ሲሆን ቴዲ አፍሮ በማረሚያ ቤቱ ሚኒባስ ተጭኖ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት አምርቷል። ሰኞ ሚያዝያ 13 ቀን ቴዲ ተመልሶ ፍርድ ቤት ይመጣል ከብይኑ በኋላም ወይ ተመልሶ ማረሚያ ቤት ይሄዳል አሊያም በዋስ ይለቀቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!