የአክብሮትና የሰማዕታት መታሰቢያ ቀናት እንደሚከበሩ ተገለጸ
ማትያስ ከተማ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ጥቅምት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. November 3, 2010)፦ የፊታችን ቅዳሜ ጥቅምት 27 ቀን 2003 ዓ.ም. (ኖቬምበር 6 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን መፈታት አስመልክቶ ”የአክብሮት ቀን” ብለው የሚያከብሩ ሲሆን፣ እሁድ ጥቅምት 28ን (ኖቬምበር 7ን) ደግሞ ምርጫ 97ን ተከትሎ ለተጨፈጨፉት የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ ሊያከብሩ ነው። በዝግጅቱ ላይ ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ ይገኛሉ።
በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን መፈታት ምክንያት በማድረግ ቅዳሜ ጥቅምት 27 ቀን 2003 ዓ.ም. (ኖቬምበር 6 ቀን 2010) ከሰዓት በኋላ ከ7 ሰዓት (13፡00 ሰዓት) ጀምሮ የአክብሮት ቀን አድርገው እንደሚያሳልፉ ታወቀ። ወ/ሪት ብርቱካን በተፈቱ ሰሞን አስቸኳይ ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ሲሆን፤ የቅዳሜው የአክብሮት ቀን የሚከበረው ደግሞ በወቅቱ የደስታው ተካፋይ መሆን ባልቻሉ ኢትዮጵያውያን አሳሳቢነትና የዝግጅቱን ኃላፊነት በበጎ ፈቃድ ለማድረግ የተነሳሱ እህቶች ከስዊድን የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ኮሚቴ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መሆኑ ታውቋል።
እሁድ ጥቅምት 28 ቀን 2003 ዓ.ም. (ኖቬምበር 7 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) ደግሞ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ድምፅ አለመከበርን ምክንያት በማድረግ አደባባይ በወጡና በየአካባቢው በተገኙ ንጹኀን ዜጎች ላይ ኢህአዴግ በወሰደው ጭፍጨፋ የተገደሉትን 193 ሰዎች በማሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰማዕታት መታሰቢያ ዝግጅት እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል።
በስዊድን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም በእሁድ ኖቬምበር 7 ቀን ከሰዓት በኋላ ከ7 ሰዓት (13፡00 ሰዓት) ጀምሮ አሉንዳ በሚገኘው የህዝብ አዳራሽ (ፎልከትስ ሑስ) ውስጥ የሰማዕታት መታሰቢያውን ዝግጅት የሚያደርጉ ሲሆን፤ ይሄንኑ አብሮ ለመካፈልና በወ/ሪት ብርቱካን የክብር ግብዣ ላይ ለመገኘት ጭምር ከዴንማርክ የሚመጡ የአንድነት ድጋፍ ኮሚቴ እህት ማኅበር አባላትም እንደሚገኙ ታውቋል።
በተጨማሪም ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ በተደረገላቸው ግብዣ መሰረት በስፍራው በመገኘት ማብራሪያና ገለጻ እንደሚያደርጉም ለመረዳት ችለናል።
ዳኛ ወልደሚካኤል ቀደም ሲል የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ፣ በኋላም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ም/ፕሬዝዳንት የነበሩ ሲሆን፣ የሰኔ አንዱና የጥቅምት 22ቱ አጣሪ ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ሲሰሩ በተለይ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ "ሪፖርቱን አስተካክሉ" የሚል ጫና ሲደርስባቸው ሐቁን ሸፍነው ለማቅረብ ህሊናቸው ስላልፈቀደ ትክክለኛውንና ያልተበረዘውን ሪፖርት እንደያዙ ከሀገር በመሰደድ በአሁኑ ጊዜ በሆላንድ ሀገር በስደት እንደሚኖሩ ይታወቃል።



