በስዊድን የሰማዕታት ቀን ተከበረ
”ያወጣው አካል ያላከበረው ሕግ እንዳልተፃፈ ይቆጠራል” ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 4 ቀን 2003 ዓ.ም. November 13, 2010)፦ ከስዊድን በዕለተ እሁድ ከጠዋቱ አራት ሰዓት (10፡00 ሰዓት) ጀምሮ የሚተላለፈው የኢትዮጵያ ድምፅ ሬድዮ የዕለቱን ዝግጅት የጀመረው ’’አይ ሽብሬ” በሚለው ለሰማዕታት ቀን መታሰቢያ በተዘጋጀው ግጥም ነበር።
አያይዞም ይሄው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የሰማዕታት ቀን በስቶክሆልም ከቀኑ 13 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያውያኑ በአንድነት አስበውት እንደሚውሉ ለቀጥታ አድማጮቹና በዓለም ዙሪያ በፓልቶክ ለሚከታተሉት አወጀ።
በዛው ሰዓት ደግሞ በስቶክሆልም የሚገኘው በደብረ ሠላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ባደረገው ማሳሰቢያ መሠረት ለሟች ወገኖች በቤተ ክርስቲያኑ አባቶችና በምዕምናን ፀሎት እየተደረገ መሆኑ ተሰማ።
የስቶክሆልምና የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ምርጫ 97 ተንተርሶ የተጨፈጨፉ ወገኖቹን በመኖሪያ ቤቱ፣ በቤተክርስቲያንና ባለበት ቦታ ሁሉ በዕዝነ ልቦናው እያሰበ አረፈደ። ከሰዓት በኋላ 7 ሰዓት (13፡00 ሰዓት) ደግሞ በአንድነት የመታሰቢያ ሥርዓት ሊያደርግ ቀጠሮ ይዟል። ሆኖም በተባለው ሰዓት አብዛኛው ታዳሚ ስላልተገኘ አርፍዶ በመድረስ የኢትዮጵያውያን ልምዳችን መሰረት ዘጠኝ ሰዓት (15፡00 ሰዓት) ሥርዓቱ ተጀመረ።
አቶ ሙሉጌታ አበበ ከቦታው የሚተላለፈውን ሙሉውን የመታሰቢያ ሥርዓት በፓልቶክ ለሚከታተሉ ወገኖች ከማስተላለፍ ጋር ደርበው የፕርግራም መሪነቱን ይዘው ስለነበር ህዝቡ በሕብረት የህሊና ፀሎት እንዲያደርግ ጠየቁ። ከፀሎቱ በኋላም የፕሮግራሙን ቅደም ተከተል በማተዋወቅ አቶ አህመድ ዓሊ በስዊድን የኢትዮጵያ ራድዮ ኃላፊ ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዙ።
አቶ አህመድ ይህ የሰማዕታት ቀን በመላው ዓለም በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በፀሎትና ሰማዕቱ የረገፉበትን ዓላማ በመከተል ቃል የሚገቡበት ቀን መሆኑን ገልጸው፤ ለዚሁም በሕብረት በመስማማት ከመታገል ውጭ ሌላው አማራጭ የትም ሊያደርስ እንደማችል በመግለጽ ንግግራቸውን ከፈቱ።
ስለዚህም ሲያስረዱ መንገዱ ላይ ቆሞ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገባ የሚከላከልን ዲያቢሎስ በአንድነት አስወግዶ ቦታውን እንደማስለቀቅ እኔ ባልኩት መንገድ ካልሆነ በስተቀር መንግሥተ ሰማያት ልንገባ አንችልም ብሎ እርስ በርስ በመጋጨት የምናመጣው ውጤት አይኖርም ብለዋል።
ቀደም ባለው የደርግ የአገዛዝ ዘመንም ዓላማቸው አንድ የሆኑ ድርጅቶች ”ከገጠር ወደ ከተማ”፤ ”የለም! ከከተማ ወደ ገጠር” በሚል የመንገድ አካሄድ ብቻ በመቃረን ሊያስወግዱ ያሰቡትን ትተው እርስ በእርስ ለመጠፋፋት ችለዋል ሲሉ ከታሪክ በመጥቀስ አስረድተዋል።
”የበይወች አለመስማማት ለተበይ ይጠቅማል” በማለት የሁለት ነብሮችን ፀብና የሚዳቋን ማምለጥ በምሳሌነት የጠቀሱት አት አህመድ፤ አሁንም የጋራ አጥቂያችንን ለማሸነፍ ኩርፊያና ሹክቻን ትተን በመነጋገር በመወያየትና በመስማማት አንተ ትበልጥ አንተ ትበልጥ ተባብለን በጋራ መሥራት ይገባናል ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ አህመድ ቀደም ሲል በቅንጀት አባላት መከፋፈል ምክንያት የደረሰውን አንስተው ሲናገሩም፤ የእነሱ በግለሰብ ደረጃ አለመስማማትና መለያየት አይተን ግለሰቦችን በመከተል መሄድ ማለት የተነሳንበትን ዓላማ መዘንጋት ነው ብለዋል። እንዲሁም በቅንጅት አባላት በፊትም ሆነ በኋላ በደረሰው ሁኔታ ተስፋ ቆርጫለሁ ብሎ ከትግል መሸሽም ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
አቶ አህመድ ንግግራቸውንም ሲያጠቃሉ፤ በዛሬው ዕለት የሰማዕታትን ቀን አስበን በፀሎት መለያየት ብቻ ሳይሆን፤ ትግላችንን ለማጠናከርና በነሱ ዓላማ ይዘን ለመጓዝ ቃል የምንገባበት ቀን ነው ብለዋል።
ቀጥለው በክብር እንግድነት በቦታው የተገኙት ዳኛ ወልደሚካኤል መሸሻ መድረኩን ያዙ። ዳኛው ለጥቂት ደቂቃ አቀርቅረው ዝም አሉ … አዎን! በዛች ደቂቃ የሚያስቡት ስለ ጭፍጨፋው ካልሆነ በስተቀር ሌላ ነገር ሊሆን እንደማችል መገመት አያዳግትም። እኝህ ሰው እንደ ህዝብ የወገኖቻቸውን እልቂት በዓይናቸው አይተው አዝነዋል። እንደ ሕግ አዋቂነታቸው ደግሞ የተሠራው ኢ-ሰብዓዊ ተግባር አንገብግቧቸዋል። በዚህ ላይ የአጣሪ ኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን አይተው ተሳቀዋል። በዝምታ ከወገኖቻቸው ፊት ወደ ውስጥ እያነቡ ቆዩ።
”በዚህ የሰማዕታት ቀን መታሰቢያ ሥርዓት ላይ ከናንተ ጋር ልገኝ በመቻሌ ደስተኛ ነኝ። በመካከላችሁ እንድገኝ በማድረጋችሁም አመሰግናለሁ! ...” በማለት ነበር ዳኛ ወ/ሚካኤል ንግግራቸውን የጀመሩት።
”ሰማዕታቱ አልሞቱም፣ የነሱ ሞት እኛን ለከፍተኛ ትግል እንድንነሳ ስላደረገ ህያው ናቸው። እነሱ ’በቃን! የምንፈልገውን መርጠናል ... ድምፃችን መከበር አለበት! …’ በማለት በድፍረትና በወኔ ተነስተው ደማቸውን አፍሰዋል። ያ ተግባራቸው አባቶቻችን በአድዋና በማይጨው የከፈሉትን መስዋዕትነትና ጀግንነት በወጣቱ ልብም ውስጥ እንዳለ ሊረዳ ያስችለዋል ...” በማለት ዳኛ ወ/ሚካኤል ንግግራቸውን ቀጠሉ …
ሆኖም ”የፃፈው አካል ያላከበረው ሕግ እንዳልተፃፈ ይቆጠራል” እንደሚባለው ሁሉ በተደጋጋሚ የራሱን ሕግና የሰው ልጅ በሰውነቱ ብቻ ሊያገኝ የሚገባውን መብት የሚገፈው የኢህአዴግ እነዚህን ንጹህ ዜጎች መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ በአደባባይ ጨፍጭፏል … አስሯል በዙዎችም ላይ የአካል ጉዳት አድርሷል” ብለዋል።
አያይዘውም ንጹኀንን በመግደል የምርጫ 97 ውጤት ለማዳፈን የተከፈተው ተኩስ ሰኔ አንድ ቀን የተጀመረ ሲሆን፣ ጋብ ብሎ ከርሞ ከጥቅምት 22 እስከ ህዳር 1 እንዲሁም ከህዳር 4 ለተከታታይ 3 ቀናት እንደዘለቀ ገልጸው፤ ሌላውን ዝርዝር በጥያቄና መልስ ወቅት እንደሚያስረዱ በማስታውቅ ንግግራቸውን ቋጩ።
በመቀጠልም ማራኪ ወይም መስከረም በመባል የምትታወቀው ገጣሚ ግድያውን የሚያወግዝና ሌላውንም ህዝብ ለትግል የሚያነሳሳ ግጥም አቀረበች። ተያይዞም በአጋዚ ሠራዊት የተጨፈጨፉትን ሰማዕታት የሚያሳዩ ሁለት ፊልሞች በተከታታይ የቀረቡ ሲሆን፣ አብዛኛውን ታዳሚ ያስለቀሱና ያስደመሙ ነበሩ።
እረፍት ከመደረጉ በፊት በሌላ ፀሐፊ የቀረበ ”ስማችን ብቻ ተወን” የሚል ግጥም ቀረበ። ይህ ግጥም ግድያና ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ እስካሁንም በኃይል የመንግሥትን ሥልጣን ጨብጠው የሚገኙት ባለሥልጣናት እንኳን ለበደሉት ህዝብ ይቅርና የራሳቸውም ወገኖች ጭምር ምን ያህል እንደሚያፍሩባቸው የሚያስረዳ ነበር።
ከእረፍት መልስ ዳኛ ወ/ሚካኤል በፊልምንና በጽሑፍ የተደገፈ የማጣራቱንና ሌላ ሌውን ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ ቢኖርም፣ አሁን ባለበት ሁኔታ ለማሳየት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ ከቤቱ ለሚጠየቅ ማናቸውም ጥያቄ መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታወቁ።
በዚህም መሰረት ከአቶ ታጠቅ ዝርዝር ሁኔታውን እንዲያስረዱ በተጠየቁት መሰረት እንደሚከተለው ገልጸውታል።
”የማጣራቱን ሥራ እንድቀበል ከአለቃዬ በትዕዛዝ መልክ ደረሰኝ። ይህንንም የማልቀበል ከሆነ ለአደጋ የተጋለጥኩ መሆኔ ተነገረኝ። በመሆኑም በኔና በቤተሰቤ ላይ መጥፎ ሁኔታ እንደተጋረጠብን ለመረዳት ቻልን። ሆኖም አማራጭ ስላልነበረኝ ሥራውን ተቀበልኩ። ምናልባትም ሰዎቹ እራሳቸውን ሊያርሙ ፈልገው ይሆናል የሚልም ሃሳብ ነበረኝ። ነገር ግን መጀመሪያ በአባልነት በኋላም የአጣሪ ኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ሆኜ ለመሥራት ላይ እንዳለሁ ከኮሚሽኑ አባላት መካከል አንዳንዶቹ ምንም የምናጣራው ሁኔታ እንደማይኖር፣ እነሱ በማጣራት መልክ በሚጽፉት ወረቀት ላይ ብቻ መፈረም እንደሚገባን ይነግሩን ጀመር። ይህን ሁኔታ ስሰማ ንዴትና ድንጋጤ ቢሰማኝም የበለጠ በማጣርራቱ ሥራ ገፍቼበት የመጣውን ሁሉ ለመቀበል ቆረጥኩ። ...
”ይህ ብቻ አልነበረም ሌሎቹ የኮሚሽኑ አባላት ይጠፉም ጀመር። ታመምን የሚሉና በልዩ ልዩ ምክንያት ሥራውንም ጥለው የሚሸሹም ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ለሥራ የሚያውክ እየሠራን ያለነውንም ሥራ የሚንድ ሃሳብ ይዘው የሚመጡና የሚበጠብጡንም ነበሩ። እንደውም ይብስ ተብሎ መርማሪዎች ተዘጋጅቶላችኋልና እነሱን ይዛችሁ ተንቀሳቀሱ ተባልን። ይህንን ልንቀበል እንደማንችል ነግረን እራሳችን መርማሪዎች የምናዘጋጅበትን ሁኔታ አመቻችተን ሥራውን ጀመርን ። ...
”በአጠቃላይ በውስጣችን ያለውን ፈታኝ ሁኔታ እየተቋቋምን የምርመራውን ሥራ ብንገፋበትም መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት ትብብር የሚያሳዩን ጥቂቶች ነበሩ። እንኳን ሌላው ቀርቶ የተጎጂ ዘመዶች እንኳን ጉዳት የደረሰባቸውን ልጆቻቸውን በፍራቻ ምክንያት ሊያቀርቡልን ፈቃደኛ አልነበሩም። ...
”ያም ሆነ ይህ ከመካከላችን ሐቀኞችና ለእውነት የቆሙ በመኖራቸው በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎች በመዘዋወር ብዙ ጉዳተኞችን ልናገኝ ችለናል። የቅንጅት አባላት በእስር የሉም የተባለበትም ቦታ በድብቅ ታስረው አግኝተናል። የ16 ዓመት ልጅ በጥይት ተመታ ግማሽ አካሏ ሽባ የሆነችንም ልጅ ቤተሰቦቿን በማግባባት ልናያት ችለናል። በአጠቃላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ አሳዛኝ ነበር። ...” በማለት እንባ እየተናነቃቸው ምርጫ 97ን ተከትሎ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ያካሄደውን ጭፍጨፋ አስረድተዋል።
”በመሰረቱ መንግሥት እናንተ በውጪ በምታድርጉት ውትወታና ግፊት እንዲሁም እርዳታ ከሚሰጡት ለጋሽ ሀገሮች የደረሰበት ተፅዕኖ ስላስጨነቀው ያደረገው እንጂ ሥራውን ያውቅ ስለነበር ማጣራቱን ፈልጎት ሳይሆን በግዱ የተቀበለው ነበር” ሲሉ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለተሰብሳቢው አስረድተዋል።
ዳኛ ወልደሚካኤል ያዩት፣ የሰሙት እና በማስረጃ አስደግፈው የያዙት ሰፊ በመሆኑ፤ ዘርዝረው ለመጨረስ ሰዓቱ ቢያንስም፤ ከብዙ በከፊሉ ይሄንን ገልጠው፤ የሰማዕታት ቀን መታሰቢያው ሥርዓት ከምሽቱ 12 ሰዓት (18፡00 ሰዓት) ተጠናቋል።



