የወ/ት ብርቱካን የአክብሮት ቀን ተከበረ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 2 ቀን 2003 ዓ.ም. November 11, 2010)፦ ባለፈው ቅዳሜ በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት የወ/ሪት ብርቱካን የአክብሮት ቀን ተከብሮ ዋለ።
በዚህ የአክብሮት ቀን ዳኛ ወ/ሚካኤል መሸሻን ጨምሮ ከዴንማርክ የመጡ የአንድነት ድጋፍ ኮሚቴ እህት ማኅበር ታዳሚዎችና የስቶክሆልምና አካባቢዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በዕለቱ አቶ ሙሉጌታ አበበም መድረኩን በመምራትና ሙዚቃ በመምረጥ የአክብሮቱ ቀኑ ፈር ይዞ እንዲጓዝ የበኩላቸውን አገልግሎት ሲያበረክቱ፤ ዳኛ ወ/ሚካኤል መሸሸና የዴንማርኩ አቶ ዮሐንስ መኮንን ንግግር አድርገዋል።
ዳኛ ወ/ሚካኤል ባደረጉት ንግግር፤ ወ/ሪት ብርቱካን በቆራጥነት ያደረገችውን ተጋድሎ አድንቀው፣ ወደ ስዊድን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያውያኑ መካከል ያዩት ሕብረትና በሁሉም መስክ ያለው የባለሙያ ብዛት የስዊድን ነዋሪዎችን ዕድለኛ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል። አክለውም ”... ለወደፊቱም በዚሁ ትብብራችሁና በማይነጥፍ ችሎታችሁ በመጠቀም ትግላችሁን ይበልጥ መቀጠል ይገባችኋል” በማለት ምክራቸውን ለግሰዋል።
አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው የወ/ሪት ብርቱካንን የአክብሮት ቀን እና በሰማዕታት መታሰቢያ ዕለት ለመገኘት ከጓደኞቻቸው ጋር ከዴንማርክ እንደመጡ አስረድተው፤ ለወሪ/ት ብርቱካን ያላቸውን ክብርና አድናቆት በመግለጽ የትግል ዓርማቸውን ይዘን መጓዝ ይገባናል በማለት አሳስበዋል። በንግግራቸው ማሳረጊያም ”ለብርቱካን ማንም ክብርና አድናቆት መስጠት ይገባዋል፤ ብርቱካንን የጠላ የሆነ ችግር ያለበት ሰው መሆን አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ የወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሣ የአክብሮት ቀን መፈታታቸው እንደተሰማ ተመሳሳይ ዝግጅት ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ሙሉ ወጭውን ሸፍነው ያዘጋጁት ወ/ሮ ቆንጅት መንገሻ ነበሩ። ያሁኑን ደግሞ ወ/ት ዜናዬ አበበ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።
በተጨማሪ ለወ/ት ብርቱካን የአበባ መግዣ የሚሆን እንላክ በማለት የዴንማርክ የአንድነት ድጋፍ ሰጪ ማኅበር አባላት ባሳሰቡት መሰረት 3300 የስዊድን ክሮነር መሰብሰቡንና ለወ/ሪት ብርቱካንም እንደሚላክ ለማወቅ ችለናል።



