ኮንሰርቱ እስከ መጪው ኅዳር ይዘልቃል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም. May 24, 2008)፦ ዛሬ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ተኩል ላይ አርቲስት ንዋይ ደበበ በአዲስ አበባ በሚገኘው ግዮን ሆቴል “ዩኒቲ ሐውስ” በተባለው ቦታ የመጀመሪያውን ኮንሰርት እንደሚያሳይ ከአዲስ አበባ የደረሰን ሪፖርት ጠቆመ።

 

በዚሁ ኮንሰርት ላይ እስከ 15 ሺህ የሚሆን ተመልካች ሊገኝ እንደሚችል የተጠቆመ ሲሆን፣ የኮንሰርቱ አዘጋጅ “አፍሪካን ሳውንድ ሪከርዲንግ ስቱዲዮ” መሆኑ ታውቋል። ዛሬ የሚጀመረው የንዋይ ኮንሰርት የሚጠናቀቀው በመጪው ኅዳር ወር እንደሆነ ለማረጋገጥ ተችሏል።

 

በዛሬው ኮንሰርት ላይ ንዋይ ሠላሳ አምስት ዘፈኖችን ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ዝግጅቱም እስከ ምሽቱ ሰባት ሰዓት (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) እንደሚዘልቅ ለመረዳት ችለናል።

 

የንዋይ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ብቻ ተጀምሮ ወደ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ጅማ ድሬዳዋ፣ ናዝሬት፣ ዝዋይ፣ አዋሣ፣ አርባምንጭ፣ ወላይታ፣ መቀሌ፣ ደብረ ብርሃን፣ ደሴ እና ደብረማርቆስ እንደሚደረግ ለማረጋገጥ ችለናል። ኮንሰርቱ በእነዚህ ከተሞች ከተካሄደ በኋላ በአዲስ አበባ ኤግዝቢሽን ማዕከል፣ በሒልተን ሆቴል እና በስታዲየም እንደሚደረግ ታውቋል። ከዚህም ሌላ በመሃል “ክብር ለሴቶች” በሚል በሚሊንየም አዳራሽ ዝግጅት እንደሚደረግ ታውቋል።

 

ይህንን ኮንሰርት ለማዘጋጀት ሁለት ዓመታትን እንደፈጀ ለመረዳት ችለናል። በግዮኑ “ዩኒቲ ሐውስ” 15 ሺህ ሰዎች በሚይዘው ቦታ ላይ የመግቢያ ዋጋ 200 የኢትዮጵያ ብር ሲሆን፣ ምግብና መጠጥ አይጨምርም። ነገር ግን በተመጣጣኝ ዋጋ ምግብና መጠጥ እንደሚዘጋጅ ታውቋል። ቪ.አይ.ፒ. (ልዩ ቦታ) ደግሞ የመግቢያ ዋጋው ብር 500 ሲሆን ቦታው አንድ ሺህ ሰው እንደሚይዝ ሲሆን፣ እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ድረስ ምግብና መጠጥ በነፃ መሆኑ ታውቋል።

 

የአፍሪካን ሳውንድ ሪከርዲንግ ስቱዲዮ መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰር የሆኑት አቶ አሌክስ ብርሃኑ ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ሲያትል ውስጥ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም በአሜሪካን ሀገር የበርካታ አርቲስቶችን ኮንሰርቶች አዘጋጅተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ፣ ቴዲ አፍሮ (ቴዎድሮስ ካሳሁን)፣ ላፎንቴኖች፣ ጊይልዶ ታደሰ፣ ሕብስት ጥሩነህ፣ አብዱ ኪያር፣ ታምራት ደስታ፣ ጥበቡ ወርቅዬ እና የሳቮድን ኮንሰርቶችን ያዘጋጁ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግን የንዋይ ደበበን ሲያዘጋጅ የመጀመሪያው እንደሆነ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ