ንዋይና ታማኝ በጋራ በስቶክሆልም የሙዚቃ ዝግጅት አሳዩ
ንዋይ ደበበ በቅርቡ አዲስ ነጠላ ዜማ እንደሚለቅ ገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2000 ዓ.ም. May 31, 2008)፦ አርቲስት ንዋይ ደበበ እና ታማኝ በየነ በአንድነት በትናንትናው ምሽት በስዊድን ዋና ከተማ ስቶክሆልም የሙዚቃ ዝግጅታቸውን ለርካታ ኢትዮጵያውያንና ለጥቂት የሌሎች ሀገር ዜጎች ሲያሳዩ አመሹ።
በስቶክሆልም “ሐሉንዳ” በተሰኘው ክፍለ ከተማ የሶሪያኖች ቤተክርስቲያን አዳራሽ ውስጥ ነበር የሙዚቃ ድግሱ የተደረገው። በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ወደ 400 የሚጠጉ የአርቲስቶቹ አድናቂዎችና የሙዚቃ ታዳሚዎች ተገኝተዋል።
ከእኩለ ሌሊት በኋላ 00፡45 ሰዓት (ለሰባት ሰዓት ሩብ ጉዳይ) ላይ ነበር ንዋይ ደበበ “እኛው እንታረቅ” በሚለው ዜማው ዝግጅቱ የተጀመረው። ንዋይ ወደ መድረኩ ሲወጣ ታዳሚው በጩኸት፣ በፉጨት፣ በጭብጨባ በመታገዝ ደማቅ አቀባበል አድርጎለታል።
በዚህ ምሽት ንዋይ ከድሮ አልበሞቹ ጀምሮ እስከ መጨረሻው አልበሙ ውስጥ ካሉት ዘፈኖቹ ውስጥ በርካታ ዜማዎችን አቅርቧል። ከእነዚህም ውስጥ ማዕበል፣ የበላይ፣ የተሞናሞነው፣ ሀገሬ እንዴት ነሽ?፣ የፍቅር ገዳም፣ ለየብቻ፣ ዳህላክ፣ የጉራጌ ልጅ፣ ወላይትኛ፣ … የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።
አርቲስት ታማኝ በየነ ወደ መድረኩ የወጣው 01፡25 ሰዓት (ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ከሃያ አምስት) ገደማ ነበር። ታማኝ ወደ መድረኩ በወጣ ጊዜ ታዳሚው በደማቅ ሁኔታ ተቀብሎታል።
ታማኝ “ዘሬ ምንድነው? - ኢትዮጵያዊ” የሚለውን ጨምሮ ጎሣዬ በመጨረሻ አልበሙ ያካተተውን የኦሮምኝ ዜማ፣ የቴዲ አፍሮን “ያስተሰርያል”፣ “ቡና” የሚሉትን ዜማዎች ተጫውቷል።
ዝግጅቱ የተጠናቀቀው ከሌሊቱ 4፡00 ሰዓት (ከሌሊቱ 10 ሰዓት) አካባቢ ሲሆን፣ ንዋይ እና ታማኝ በጋራ በዘፈኑት “የአንገት ሐብል” በሚለው ነበር። ንዋይ በቅርቡ አዲስ ነጠላ ዜማ እንደሚለቅ ለሙዚቃ አፍቃሪዎቹ በዚህ መድረክ ላይ ገልጾላቸዋል።
በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ የመግቢያ ዋጋው 250 የስዊድን ክሮነር ነበር።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዘጋቢ ያነጋገራቸው የሙዚቃ ድግሱ ታዳሚዎች በዝግጅቱ በተለይም በንዋይ ደበበ እና በታማኝ በየነ መደሰታቸውን ገልጸዋል። አንዲት የንዋይ ደበበ አድናቂ የወርቅ አንገት ሐብል እና የአልማዝ ቀለበት ለንዋይ መድረክ ላይ አበርክታለታለች።