ያልተሳካው የንዋይ ደበበ ኮንሰርት
Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2000 ዓ.ም. May 25, 2008)፦ ትናንት ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2000 ዓ.ም.፣ ንዋይ ደበበ በግዮን ሆቴል ኮንሰርት እንደሚያቀርብ ስሰማ በጉጉት ወደዚያው አመራሁ። በግዮን ከተደረጉ ኮንሰርቶች የቅርብ ትዝታዬ የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ነበርና ከሱ ልምድ ወስጄ በጊዜ ወደ ሆቴሉ አመራሁ። አብሬ ልገባ የተቃጠርኩዋቸው ጉዋደኞቼም “ሰልፍ ይዘህ፣ ትኬት ቆርጠህ ጠብቀን” ሲሉ ከውሃ የወፈረች መልዕክታቸውን በስልኪቱ አስተላለፉልኝ።
ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲል ደረስኩ። ምንም ሰልፍ ካለመኖሩ የተነሳ ተራ እንዲያስጠብቁ የተመደቡ በርካታ ጠብደሎች ቆመው ወጋቸውን ይጠርቃሉ። ቴዲ አፍሮ በዚህ ቦታ ኮንሰርቱን ሲያቀርብ የነበረው ግርግር ታወሰኝና “በሉ ስትገቡ ቁረጡ ምንም ሰልፍ የለም” ብዬ ለጓደኞቼ ደወልኩላቸውና ወደ ውስጥ ዘለቅኩ።
የቅንጅቱ ኢንጂንየር ግዛቸው ልጅ የሆነው ታዋቂው ዲጄ ፋትሱ መድረኩን ተቆጣጥሮታል። የሚከለክል፣ የሚጋፋ፣ የሚያስቆም፣ የሚሸፍን ስላልነበረ ቀጥ ብዬ ወደ መድረኩ ዘለቅኩ። ለኮንሰርቱ ቦታው ከሚይዘው 15 ሺህ ሰው ሩብ ያህሉ እንኳን ስላልነበረና ጥሩ ስሜት ስላልተሰማኝ የሚበላና የሚጠጣ ፍለጋ አመራሁ።
ግራና ቀኝ ምግብና መጠጡን ያዘጋጀው የግዮን ሆቴል አስተናጋጆች አነስ አነስ ባሉ ድንኩዋኖች ውስጥ የስጋ ጥብስና መጠጥ ደርድረው ይሸጣሉ። ጥብስ ለመግዛት ትኬት ሳስቆርጥ 60 የኢትዮጵያ ብር ተጠየቅሁ፤ “መቼስ ምን አደርጋለሁ አንዴ መጥቻለሁ” ብዬ ከፈልኩ። በ60 ብር የገዛሁትን ጥብስ ግማሹን ድንች ጥብስ ሞልተው ሁለት አምፕሲሊን የምታካክል ትንንሽ ዳቦ ጣል አደረጉልኝ። ባፌ ባልናገርም “ይቺን ነው እንዴ የሚሰጡኝ?!” ስል እያጉረመረምኩ የሚጠጣ ፍለጋ ዞር ዘር አልኩ። የመጠጡም ዋጋ ቀላል አልነበረም። ውጭ ቢሆን 2 ብር ከሃምሳ ሣንቲም ገዝቼ የምጠጣውን ውሃ 15 ብር ገዝቼ ወደ ኮንሰርቱ አመራሁ።
የሰዉ ቁጥር የጨመረ አይመስልም። እንዳውም አብዛኛው ሰው ሣሩ ላይ ተቀምጦ የየራሱን ይጫወታል። ከምሽቱ 3 ሰዓት ሲሆን ንዋይ ወደ መድረኩ ሊመጣ እንደሆነ ተነገረና ሁሉም ሰብሰብ ማለት ጀመረ። እንደዛም ሆኖ ግን በጠቅላላ የነበረው ተመልካች ከ3 ሺህ አይበልጥም ነበር።
ንዋይ ነጭ በነጭ ለብሶ “ሃገሬን አልረሳም” እያለ ወደ መድረኩ ብቅ ሲል የተገኘው ሰው አጨበጨበለት፣ አበባ ተበረከተለት፣ ሪችት ተተኮሰለት። እሱም እንኳን አደረሳችሁ! እያለና አበባውን እየበተነ “ከበረከቱ ተቋደሱ” በማለት አበባውን በተነው። ዝግጅቱ የሙዚቃ ኮንሰርት ሳይሆን የቤተሰብ በዓል መሰለ። ”ሃገሬን አልረሳም” የሚለውን ዘፈን ሲዘፍን እጆቹን ዓይኑ ላይ አድርጎ እንደማልቀስ ሲል አንዱ ጉዋደኛዬ “ይሄኔ እኮ ሰው ለምን አልገባም ብሎ ነው የሚያለቅሰው” ሲል ቀልዷል።
35 ዘፈኖች ያቀርባል የተባለው በ5 ዘፈን ድምጡ ተዘጋ። ከባንዱ ጋር እስኪስማማ እንደሆነ የገለጠና በኋላ ላይ እየተስተካከለ ቢመጣም በአጠቃላይ የዘፈነው 16 ዘፈኖችን ብቻ ነበር።
በኮንሰርቱ ላይ በርካታ ሰው አለመገኘቱ ለኮንሰርቱ ድምቀት ነስቶታል። በተጨማሪም በየመሃሉ በመድረክ አስተዋዋቂዎቹ የሚነገረው ከ16 ዓመት በኋላ የንዋይ ሀገሩ መግባት ለሀገሩና ለህዝቡ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ በተደጋጋሚ ሲገለጥና በተደጋጋሚ የስፖንሰር አድራጊዎች ስም ሲጠራ መሰማቱ ገንዘብ ከፍለንበት የገባነው የሙዚቃ ኮንሰርት ሳይሆን በነፃ የተዘጋጀ ነበር የሚመስለው።
በየመሃሉም ሌሎች ዝግጅቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ዘመን ያፈራቸው 15 የሚሆኑ ወጣት አርቲስቶች ለንዋይ ክብር ስንል በማለት አንድ ዘፈን አጅበውት ዘፍነዋል።
ዝግጅቱ ከሌሊቱ 8 ሰዓት ሲጠናቀቅ የቴዲ አፍሮን ደማቅ ኮንሰርት በማስታወስ እየተጽናናሁ ግቢውን ጥዬ ወጣሁ።