በዶ/ር ታዬ ይመራ የነበረው አንጋፋው ኢመማ ለመጨረሻ ጊዜ ተዘጋ
አዲሱ/ተለጣፊው መምህራን ማኅበር የ12 ሚሊዮን ብር ሊወርስ ነው
Ethiopia Zare (ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2000 ዓ.ም. June 27, 2008)፦ ለሰላሳ ዘጠኝ ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲንቀሳቀስና በአንድ ወቅት በዶ/ር ታዬ ወ/ሠማያት ይመራ የነበረው አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ከ15 ዓመታት የፍርድ ቤት ሙግት በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ በሰበር ችሎት እንዲዘጋ ተወሰነ። አዲሱ/ተለጣፊው የመምህራን ማኅበር ወደ 12 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ወራሽ ሊሆን ነው።
ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት በቀድሞው እና “ተለጣፊው” እየተባለ በብዙዎች ዘንድ በሚታወቀው በአዲሱ መምህራን ማኅበር የተጀመረው ክርክር ከፍርድ ቤት ፍርድ ቤት በይግባኝ ሲገለባበጥ ከቆየ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ በትናንትናው ዕለት በሰበር ሰሚ ችሎት በስድስት ጃኞች ውሳኔ አግኝቷል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለአዲሱ/ተለጣፊው መምህራን ማኅበር ወስኖ የቀድሞ መምህራን ማኅበር ንብረት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ወጥቶበት የነበረ በመሆኑ አንጋፋው የመምህራን ማኅበር ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቅርቧል። ሰበር ሰሚ ችሎቱ ጉዳዩን ለማየት ለሐምሌ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ የበረ ሲሆን፣ ቀጠሮውን ሰብሮ በትናንትናው ዕለት በሰበር በማየት ትዕዛዙን ያፀና ሲሆን፣ በአቶ አንተዬ ከበደ የሚመራው አዲሱ መምህራን ማኅበር በፍትህ ሚኒስቴር የተረጋገጠ ሰርተፍኬት ስላለው የአንጋፈው መምህራን ማኅበር ወራሽ ሆኗል።
ዶ/ር ታዬ ወ/ሠማያት ለማኅበራቸው ሳያሳውቁ ይመሩት የነበረውን አንጋፋውን ኢመማን ጥለው የቀድሞውን ቅንጅት በስደት ተቀላቅለው የቅንጅት ዓለምአቀፍ ካውንስል (ኪስ) መሪ ከሆኑ በኋላ የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ጐሞራው ካሣ ማኅበሩን ሲያንቀሳቅሱ እንደነበር ይታወቃል። አቶ ጐሞራው ካሣ እንዳስረዱት አንጋፋው የመምህራን ማኅበር በመዝገብ ቁጥር 25ኛ ተመዝግቦ ሰርተፍኬት አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እያለ በ1986 ዓ.ም. በመዝገብ ቁጥር 161 ለተመዘገበው አዲስ መምህራን ማኅበር የመምህራኑን ንብረት እንዲወርስ መደረጉ አግባብ አይደለም ብለዋል። በሀገሪቱ ሕግ ተቀባይነት የሌለው ሕጋዊ ሰርተፍኬታችን ሳይሰረዝ ሕልውናችን ሳይጠፋ በሌላ ሰው ስም እንዲመዘገብ መደረጉ የሕግ ግድፈት እንዳለበት፣ “አዲስ ማኅበር አደራጅተውና አቋቁመው፣ አዲስ የምዝገባ ቁጥር ከተሰጣቸው በኋላ ንብረታችንን ለመውሰድ ቀድሞውኑ የተመሰረተ ማኅበር ነው" ሲሉ መከራከራቸውን አቶ ጐሞራው ጠቅሰው፤ ከዚህ ሁሉ በኋላ በመጨረሻ በሰበር መረታታቸውን ተናግረዋል።
አዲሱ/ተለጣፊው መምህራን ማኅበር ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቷል አንጋፋው የመምህራን ማኅበር ግን አልጠራም በሚል ውሳኔ እንደተሰጠባቸው የገለጹት አቶ ጐሞራው ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ሲጠሩ “ሕገወጥ ናችሁ” መባላቸውን አረጋግጠዋል።
አቶ ጐሞራው አያይዘው እንደገለጹት ፍርድ ቤት የወሰነብን ንብረታችንን ለአዲሱ መምህራን ማኅበር እንድናስረክብ ነው። ያ ማለት በደርግ ጊዜ አንበሳ ግቢ ፊት ለፊት ዘመቻ መምሪያ እየተባለ ይጠራ የነበረው ግቢ የነሱ እንደነበር እና ቤቱን የደርግ መንግሥት ስለፈለገው በልዋጭ ብሔራዊ ቲያትር አካባቢ ብሔራዊ ባንክ ጎን ያለው ቤት ተሰጥቷቸው እስከአሁን ንብረታቸው እንደነበር አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ያለው ቢሯቸው በገንዘብ ቢተመን ወደ 3 ሚሊዮን ብር እንደሚያወጣ፣ 800 ሺህ ብር ከቢሮ ኪራይ የሰበሰቡት ገንዘብ እንዳላቸው፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሥራ ማስኬጃ፣ የመረዳጃ አገልግሎት እና አባላቱ ጡረታ ሲወጡ የሚወስዱት የተቀመጠ 5 ሚሊዮን ብር፣ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ቆማ የነበረችና አሁን የት እንደደረሰች የማትታወቀቅ ቶዮታ በአጠቃላይ ሁለት መኪኖች፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ የቤተመጻሕፍት መጻሕፍት በአጠቃላይ ግምቱ ወደ 12 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከአዲስ አበባው ቢሯቸው ብቻ እንዲያስረክቡ እንደተወሰነባቸው አቶ ጐሞራው ተናግረዋል።
ይህ በየዞኑ ያሉትን የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ገንዘብን፣ ሕንፃዎችን እና ሆስቴሎችን እንደሚጨምር ገልጸው፣ በየክፍለ ሀገሩ ያለው ገንዘብና ንብረት ቢተመን በርካታ እንደሚሆን አቶ ጐመራው አረጋግጠዋል።