Athlete Tirunesh Dibaba(ተጨማሪ ዘገባ የታከለበት)

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. July 11, 2008)፦ ዛሬ (ሐምሌ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. July 11, 2008) ማምሻውን በጣሊያን ዋና ከተማ ሮም ላይ በተካሄደው የጎልደን ሊግ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ የ5,000 ሜትር ውድድር በሴቶች የ22 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ፣ በወንዶች ደግሞ አትሌት ስለሺ ስኅነ በአንደኝነት አጠናቀቁ።

 

በሴቶች

አትሌት ጥሩነሽ 5 ሺህ ሜትሩን ያጠናቀቀችው በ14፡36፡58 ደቂቃ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በፊት በኖርዌይ ዋና ከተማ ኦስሎ በተደረገው በዚሁ ርቀት የዓለምን ክብረ ወሰን በ14፡11፡15 ደቂቃ መስበርዋ ይታወሳል።

 

በዚሁ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ መሰለች መልካሙ በ14፡38፡78 ደቂቃ ሁለተኛ፣ የጥሩነሽ እህት የሆነችው አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ በ15፡09፡93 ደቂቃ በስድስተኛ፣ አትሌት አህዛ ኪሮስ ደግሞ በ15፡13፡35 ደቂቃ በስምንተኛ በመሆን አጠናቅቀዋል። በውድድሩ ላይ ኤርትራን በመወከል የተሳተፉት አትሌት ስምረት ሱልጣን በ15፡47፡70 ደቂቃ በመግባት 12ኛ፣ አትሌት ምዕራፍ ባህታ ደግሞ 15፡58፡31 ደቂቃ ውድድሩን በ15ኛነት አጠናቅቀዋል።

 

በዚህ በያዝነው የአውሮጳውያን 2008 ዓ.ም. ከፍተኛ ድል ይጎናጸፋሉ ተብለው ከሚጠበቁት አትሌቶች ውስጥ አንዷ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ስትሆን፣ በሮሙ የጎልደን ሊግ ሁለት እህቶችዋ አትሌት እጅጋየሁ ዲባባ እና ገንዘቤ ዲባባ ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።

 

አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እ.ኤ.አ. ሴፕቴምበር 16 ቀን 2006 በአቴንስ ኦሎምፒክ በ3 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ እ.ኤ.አ. ማርች 30 ቀን 2008 ኤደንበርግ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 ቀን 2008 በአዲስ አበባ የ16ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ በ10 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ እ.ኤ.አ. ኦገስት 13 ቀን 2005 በፊንላንድ ሄልስንኪ በ5 ሺህ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ፣ ... እንዲሁም በርካታ ውድድሮችን በአሸናፊነት የተወጣች ወጣት ሴት አትሌት እንደሆነች ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለወጣት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እንዲሁም በዚህ ጎልደን ሊግ ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሙሉ መልካም ዕድል ይገጥማቸው ዘንድ ልባዊ ምኞቱን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል።

 

በወንዶች

በወንዶች የ5000 ሜትር ርቀት አትሌት ስለሺ ስኅነ በ13፡04፡94 ደቂቃ ኬንያዊውን ኤሉድ ኪፕቾጌን እና ታሪኩ በቀለን አስከትሎ ውድድሩን በአንደኝነት አጠናቅቋል። የቀነኒሳ በቀለ ወንድም የሆነው ታሪኩ በቀለ ሦስተኛ የወጣው ውድድሩን በ13፡06፡00 ደቂቃ በመጨረስ ነው።

 

በ5000 ሜትሩ ከአንደኛ እስከ 10ኛ ማንንም ጣልቃ ሳይስገቡ ውድድሩን ያጠናቀቁት ጎረቤታም ሀገሮቹ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ናቸው። 4ኛ፣ 5ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ የወጡት ኬንያውያን ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያዊውያኖቹ አትሌት ዓሊ አብዶሽ በ13፡06፡93 ደቂቃ 6ኛ፣ አትሌት በቃና ዳባ በ13፡21፡15 ደቂቃ 9ኛ፣ አትሌት ማርቆስ ገነቲ በ13፡26፡28 ደቂቃ 10ኛ፣ አትሌት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም በ13፡36፡67 ደቂቃ 12ኛ፣ አትሌት የማነ መርጋ በ13፡49፡17 ደቂቃ 16ኛ ሆነው ውድድሩን አጠናቅቀዋል። አትሌት ጥላሁን ረጋሳም በዚሁ ርቀት ላይ የተሳተፈ መሆኑ ታውቋል።

 

በወንዶች በ3000 ሜትር መሰናክል አትሌት ናሆም መስፍን በ8፡21፡09 ደቂቃ ውድድሩን በመጨረስ አምስተኛ ወጥቷል። በዚሁ ውድድር አትሌተ ሮባ ጋሪ ተሳታፊ ነበር። በ1500 ሜትር አትሌት ደሬሣ መኮንን ውድድሩን በ3፡34፡59 ደቂቃ ጨርሶ 11ኛ ወጥቷል።

 

2008 ጎልደን ሊግ

የ2008 የጎልደን ሊግ ውድድር የተጀመረው በጀርመን በርሊን ጁላይ 1 ቀን 2008 እ.ኤ.አ ሲሆን ጁላይ 6 ቀን 2008 በኖርዌይ ኦስሎ መካሄዱ አይዘነጋም። የፊታችን ዓርብ ጁላይ 18 በፈረንሣይ ፓሪስ፣ ጁላይ 29 በስዊዘርላንድ ዙሪክ ይቀጥልና ሴፕቴምበር 5 በቤልጂየም ብራስልስ እንደሚካሄድ ታውቋል።

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ