ጥሩነሽ ዲባባ የኦሎምፒክ ክብረወሰን በመስበር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘች

Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 9 ቀን 2000 ዓ.ም. August 15, 2008)፦ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ በተደረገው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የኦሎምፒክን ክብረወሰን በመስበር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
በኢትዮጵያዊቷ አትሌት ደራርቱ ቱሉ በርቀቱ ተይዞ የነበረውን 30፡17.49 ደቂቃ የኦሎምፒክ ክብረወሰነ፤ ዛሬ ጥሩነሽ 29፡54.66 ደቂቃ በመግባት አሻሽላዋለች። ሁለተኛ የወጣችው ቱርካዊቷ ኤልቫን አቢ ለገሰ ስትሆን በ29፡56.34 ደቂቃ ውድድሩን ጨርሳ ለብር ሜዳሊያ በቅታለች። አቢ ለገሰ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ስትሆን፣ በዜግነት ግን ቱርካዊ መሆኗ ይታወቃል። ሦስተኛ በመውጣት የነኀሱን ሜዳሊያ ያገኘችው የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካዋ ሻላኔ ፍላናጋን ውድድሩን በ30፡22.22 ደቂቃ በመጨረስ ነው።
አትሌት ጥሩነሽ ባስገኘችው የወርቅ ሜዳሊያ ኢትዮጵያ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ ከሕንድ እና ታይላንድ ጋር በመሆን የ25ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አስችሏታል። የኦሎምፒክ አዘጋጅዋ ቻይና በ26 የወርቅ፣ በ9 የብር፣ በ6 የነኀስ፤ በአጠቃላይ በ41 ሜዳሊያዎች የአንደኝነት ደረጃን ይዛ ትገኛለች። ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ደግሞ በ14 የወርቅ፣ በ13 የብር፣ በ19 የነኀስ በድምሩ በ46 ሜዳሊያዎች በሁለተኛ ደረጃነት ትከተላለች።
በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እጅጋየሁ ዲባባ (የጥሩነሽ ዲባባ እህት) በ31፡22.18 ደቂቃ 14ኛ ስትወጣ፣ አትሌት መስታወት ቱፋ ደግሞ ውድድሩን ሳትጨርስ ቀርታለች።
የ10 ሺህ ሜትር የሴቶች ሩጫ የዓለም ክብረወሰን 29፡31.78 ደቂቃ ሲሆን፣ የተያዘው በቻይናዊቷ ዋንግ ዩንሲያ ነው። ዋንግ ክብረወሰኑን የሰበረችው እ.ኤ.አ. 1993 ነው።
የወንድች የ10 ሺህ ሜትር ርቀት የፍፃሜ ውድድር የፊታችን እሁድ ነኀሴ 11 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 17, 2008) በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ 11፡45 ሰዓት ላይ ይካሄዳል። (ውድድሩን ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድና ቀሪዎቹን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድር ለመከታተል ይረዳዎ ዘንድ ያዘጋጀነውን የውድድሩን የጊዜ ሠሌዳ እዚህ በመጫን ያገኙታል!)



