ጥሩነሽ ዲባባ ሁለተኛዋን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘች

Ethiopia Zare (ዓርብ ነኀሴ 16 ቀን 2000 ዓ.ም. August 22, 2008)፦ ዛሬ በቤጂንግ ኦሎምፒክ በተደረገው የሴቶች 5 ሺህ ሜትር ርቀት ፍፃሜ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ አንደኛ በመውጣት ለራስዋ ሁለተኛውን፣ ለኢትዮጵያ ደግሞ ሦስተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች። አትሌት መሠረት ደፋር ደግሞ ሦስተኛ በመውጣት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የነኀስ ሜዳሊያ አስገኝታለች።
በ5 ሺህ ሜትር ዛሬ የተወዳደሩት ሦስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሲሆኑ፣ አትሌት ጥሩነሽ ውድድሩን በ15፡41.40 ደቂቃ በአንደኝነት ስትጨርስ፣ መሠረት ደፋር በ15፡44.12 ደቂቃ ውድድሩን በሦስተኝነት አጠናቃለች።
በኢትዮጵያውያኖቹ መሃል የገባችው በትውልድ ኢትዮጵያዊት፣ በዜግነት ቱርካዊት የሆነችው ኤልቫን አብይ ለገሠ ስትሆን፣ ውድድሩን በ15፡42.74 ደቂቃ አጠናቃለች።
ሦስተኛው ኢትዮጵያዊት አትሌት መሰለች መልካሙ ውድድሩን በ15፡49.03 ደቂቃ በማጠናቀቅ ስምንተኛ ወጥታለች።
ኢትዮጵያ በሦስት ወርቅ፣ በአንድ ብር እና በአንድ የነኀስ ሜዳሊያ በቤጂንጉ ኦሎምፒክ ከተሳተፉት ሀገሮች በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በ22ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የሜዳሊያ ሰንጠረዡ ደረጃ የፍፃሜ ውድድሮች በተካሄዱ ሰዓት የሚቀያየሩ መሆናቸው ይታወቃል።
ዓርብ ነኀሴ 9 ቀን 2000 ዓ.ም. (August 15, 2008) በቤጂንጉ ኦሎምፒክ በተደረገው የሴቶች 10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ የኦሎምፒክን ክብረወሰን በመስበር ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውርቅ ሜዳሊያ ማስገኘትዋ አይዘነጋም።
በሴቶች 5,000 ሜትር ርቀት የዓለም ክብረወሰን ያለው በአትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ኦስሎ ኖርዌይ ላይ ያስመዘገበቸው 14:11.15 ደቂቃ ነው። የኦሎምፒክ ክብረወሰን ደግሞ በሩማኒያዊቷ ጋብረኤላ ዛቡ ስድኒ አውስትራሊያ ላይ የተመዘገበው 14:40.79 ደቂቃ ነው።



