በኢንተርኔት አገልግሎት የንግዱ ማኅበረሰብ ተማረረ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ታህሳስ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. December 24, 2008)፦ ካለፈው ሣምንት አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት መጠቀም እንዳስቸገራቸውና በሥራቸው ላይ እንቅፋት እንደተፈጠረባቸው በአዲስ አበባ የሚኖሩ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ምሬታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።
በኢትዮጵያ በብቸኝነት (በሞኖፖል) የኢንተርኔት አገልግሎት እየሠጠ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ባጋጠመው ብልሽት ምክንያት እንደሆኑ የገለጹት እነዚሁ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት፤ “ኢ-ሜይላችንን እንኳን መክፈትና ከቀሪው ዓለም ጋር መገናኘት አልቻልንም” በማለት ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።
በተለይም በአስመጪና ላኪ (Import & Export) የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች የዚህ የኢንተርኔት ችግር ከጎዳቸው የማኅበረሰቡ ክፍሎች ውስጥ በቀዳሚነት ሊጠቀሱ እንደሚችሉ ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ ከላከልን ዘገባ ለመረዳት ችለናል።
ካለፈው ሣምንት አጋማሽ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ድረ ገጾችን ለመክፈት እጅግ እንደሚንቀረፈፍና፣ የተከፈቱትም ድረ ገጾች ላይ ተለቅ ያሉ ፎቶግራፎች እንደማይከፈቱ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ያጋጣመውን ብልሽት በቅርቡ ለማስተካከል ጥረት እያረደገ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር አክሎ ዘግቧል።



