ኮማንድ ፖስቱ ትናንት ሁለት ተጨማሪ ጋዜጠኞቸን አሰረ
ኢትዮጵያ ዛሬ (ቅዳሜ ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 19, 2016)፦ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት አዘጋጅ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና አናንያ ሶሪ ትናንት አርብ ኅዳር ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. ኮማንድ ፖስቱ ማሰሩን ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ አስረዳ። ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በማኅበራዊ ድረገጾች ላይ በመሳተፋቸው መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
እንደ ኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጻ ከሆነ፣ የታሰሩበት ምክንያት ሰሞኑን እየሰጡት ባለው አስተያየትና በፌስ ቡክ ላይ ባወጡት ፎቶግራፍ ሲሆን፤ በፎቶግራፉ ላይ እጆቻቸውን አጣምረው በመታየታቸው እንደሆነ ታውቋል። እንዲህ ያለውን ምልክት ማሳየት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መከልከሉ አይዘነጋም።
ሁለቱም ጋዜጠኞች በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች፣ በማኅበራዊ ድረ ገጾች እና ራዲዮኖች ላይ መጣጥፎችን በማቅረብና አስተያየት በመስጠት ይታወቃሉ። ጋዜጠኛ ኤልያስ ያዘጋጀው የነበረውና ተወዳጅነት አትርፎ የነበረው አዲስ ጉዳይ መጽሔት በመንግሥት ጫና ከሕትመት ውጭ እንዲሆን ሲገደድ የመጽሔቱ ጋዜጠኞች አገር ለቀው ለመውጣት ተገደዋል።
ከአዲስ ጉዳይ መጽሔት መዘጋት በኋላ፤ ጋዜጠኛ ኤልያስ ”አዲስ ገጽ” የተሰኘ መጽሔት የተሰኘ መጽሔት ማሳተም ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፤ የመጽሔቱ በሕትመት ላይ እንዳይኖር ከፍተኛ የመንግሥት ጫና ስለተደረገበት ሕትመቱ መቆሙ ይታወቃል።
ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ፤ በቅርቡ የፋና ራዲዮው ጋዜጠኛ በሩክ ከበደ በሚያዘጋጀው ሞጋች በተሰኘው ዝግጅት ላይ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በተደረገ ውይይት ጠንከር ያሉ በገዥው ፓርቲ ላይ መሰንዘሩ አይዘነጋም።
ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ፤ ፖሊስ ጋዜጠኞቹ ለምን እንደታሰሩ የገለጸው ነገር የለም።