ኮማንድ ፖስቱ በመላ አገሪቱ 11 ሺህ 607 አስሬያለሁ እያለ ነው
"የታመኑት 11 ሺህ 607 ከሆኑ ያልታመኑት ስንት ሊሆኑ ነው" አስተያየት ሰጪዎች
Ethiopia Zare (ዓርብ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. November 11, 2016):- ኮማንድ ፖስቱ 11 ሺህ 607 ሰዎችን በመላው አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማሰሩን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ መግለጹን ፋና ዘገበ።
በዚህ የፋና ዘገባን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ዛሬ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች “የታመኑት 11 ሺህ 607 ከሆኑ ያልታመኑት ስንት ሊሆኑ ነው” የሚል ጥያቄ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኮማንድ ፖስቱ በስድስት ማዕከላት 11 ሺህ 607ቱን እስረኞች ማሰሩ ታውቋል። ኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ያሰረው በጦላይ ማዕከል ሲሆን፣ ከቄለም ወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከምዕራብ አርሲ፣ ከምስራቅ ሸዋ ዞኖች 4193 ወንዶች እና 136 ሴቶችን በድምሩ 4 ሺህ 329 ሰዎችን አስሯል። ዝቅተኛ የታሳሪዎች ቁጥር ያለው በአዲስ አበባ ሲሆን፣ 393 ወንዶች እና 17 ሴቶች በድምሩ 410 መሆናቸውን ፋና ዘግቧል።
ፋና ባስተላለፈው ዘገባ የእስረኞቹ ቁጥር ዝርዝር ከዚህ በታች ይገኛል።
1. በአዋሽ ማዕከል፦ ከፊንፊኔ ዙሪያ፣ ከሰሜን ሸዋ፣ ከምስራቅ ሸዋ ዞኖች (ወንድ - 1 ሺህ 172 ሴት 2 ድምር 1 ሺህ 174)
2. በጦላይ ማዕከል፦ ከቄለም ወለጋ፣ ከአርሲ፣ ከምዕራብ አርሲ፣ ከምስራቅ ሸዋ ዞኖች (ወንድ 4 ሺህ 193 ሴት 136 ድምር 4 ሺህ 329)
3. በዝዋይ አላጌ ማዕከል፦ ከጉጂ፣ ምዕራብ ሀረርጌ፣ ምስራቅ ሀረርጌ፣ ከጉጂ ዞኖች (ወንድ 2 ሺህ 957 ሴት 91 ድምር 3 ሺህ 048)
4. በዲላና ይርጋለም፦ ከጌዲኦ አካባቢ (ወንድ 2 ሺህ 104 ሴት 10 ድምር 2 ሺህ 114)
5. በባህር ዳር ማዕከል፦ ከሰሜን ጎንደር፣ ከደቡብ ጎንደር፣ ከምስራቅ ጎጃም፣ ከአዊ ዞኖች (ወንድ 441 ሴት 91 ድምር 532)
6. በአዲስ አበባ ማዕከል፦ ከአዲስ አበባ የተያዙ (ወንድ 393 ሴት 17 ድምር 410)