Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም 2 ቀን 2002 ዓ.ም. September 12, 2009)፦ “የህዝብ መንፈሥ በማናወጥ” ህዝብ የመንግሥትን ደንብ እንዳይቀበል በማድረግ በሚል ክስ ጥፋተኛ የተባለው የ“ሠለፊያ” ጋዜጣ ባለቤትና ዋና አዘጋጅ አንድ ዓመት ተፈረደበት።

 

ጋዜጠኛ ኢብራሂም መሐመድ ጥር 23 እና 30 ቀን 2000 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣው ላይ “የእስራኤል መንግሥት ከሴኩላሪዝም ወደ ይሁዳዊነት፤ ት/ሚኒስቴር ከሴኩላሪዝም ወዴት?” የሚል ርዕስ ባለው ጽሑፍ ለአንድ ዓመት እሥራት የተዳረገ ሲሆን፤ ጽሑፉ ከተሳታፊ የመጣለት መሆኑን ገልጾ ቢከራከርም የልደታ ፍርድ ቤት ነሐሴ 18 ቀን 2001 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጥፋተኛ ብሎታል።

 

በት/ቤቶች ውስጥ ተሰባስቦ ሶላት መስገድንና ሒጃብን በሚከለክለው ረቂቅ ሕግ መሠረት የተፈረደበት ጋዜጠኛ ኢብራሂም በሌላ ተጨማሪ ክስ ለጥቅምት 2002 ተቀጥሯል።

 

ረቂቅ ሕጉ ተቃውሞ አስነስቶ ከወራት በፊት በአዲስ አበባ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲ ሙስሊም ተማሪዎች ያልተፈቀደ ሠላማዊ ሰልፍ አድርገው የነበረ ሲሆን፣ ሰልፉ በኃይል ተበትኖ ቀንደኛ አስተባባሪ የነበሩ የተባሉት መታሰራቸው ይታወሳል።

 

ረቂቅ ሕጉን በተመለከተ የተለያዩ የሙስሊም ተቋማት የተቃውሞ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይፋዊ በሆነ መልኩ እስከ አሁን ድረስ ሕጉ አለመጽደቁ ታውቋል።

 

ጋዜጠኛ ኢብራሂም መሐመድ የ8 ቤተሰቦች አስተዳዳሪ ሲሆን፣ ጋዜጣውን ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ለ10 ዓመታት የሠለፊያ ጋዜጣ አዘጋጅ ሲሆን፣ የጋዜጣውን 10ኛ ዓመት ነሐሴ 21 ቀን በእስር ቤት አሳልፏል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰይፈ ነበልባል የቀድሞ ጋዜጠኛ በተመሳሳይ የአንድ ዓመት እስራት ተፈረዶበት ወህኒ ወርዷል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ