ለሽያጭ የተዘጋጀው ኢትዮ ቴሌኮም ገቢው እየጨመረ ነው
ኢትዮ ቴሌኮም
በአፍሪካ በደንበኞች ቁጥር ይመራል
ኢዛ (ሐሙስ ጥቅምት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 17, 2019):- በከፊልና ሙሉ ለሙሉ በሽያጭ ለግል ኩባንያዎች ከሚሸጡ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በቀዳሚነት የተቀመጠው ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ደምበኞቹን ቁጥር ከ51 ሚሊዮን በላይ ሲያደርስ፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት (በሦስት ወር) ጊዜ ውስጥ ከ10.1 (አሥር ነጥብ አንድ) ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ችሏል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ዛሬ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሠጡት መግለጫ፤ ድርጅቱ በ2011 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት (በመጀመሪያው ሩብ ዓመት) ውስጥ ካገኘው ገቢ ጋር ሲመሳከር የዚህ ዓመቱ የ21 በመቶ ብልጫ አለው።
ኢትዮ ቴሌኮም የሞባይል ደንበኞቹን ቁጥር ከ51 ሚሊዮን በላይ ማድረሱ በዚሁ መግለጫ ላይ የተገለፀ ሲሆን፣ የደንበኞቹን ቁጥር ማሳደጉና የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠት የተሠሩ ሥራዎች ለገቢው መጨመር አስተዋጽኦ ነበረው ተብሏል።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት በአፍሪካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ የቴሌኮም ኩባንያዎች በአንድ አገር ውስጥ ያላቸው ደምበኞች ቁጥር፤ ኢትዮ ቴሌኮም ካሉት ደምበኞች ያነሰ መኾኑን ነው። ይህም ኢትዮ ቴሌኮም በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ ደንበኞች ያለው ኩባንያ ያደርገዋል።
ምንም እንኳን ድርጅቱ የተሻለ አገልግሎት ለመሥጠት ጥረት እያደረግኹ ነው ቢልም፤ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሞባይልና የኢንተርኔት (ዳታ) አገልግሎት የሚቆራረጥ ከመኾኑም በላይ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁለቱንም አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ እንደኾነ የከተማሪው ነዋሪዎች በማማረር ይናገራሉ። (ኢዛ)



