ETHIOPIAN HUMAN RIGHTS COUNCIL

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

መንግሥት ሕጋዊና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን ሕይወትና መብታቸውን ሊያከብረና ሊያስከብር ይገባል!

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. October 28, 2019)፦ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ (ኢሰመጉ)፤ “መንግሥት የዜጎችንን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ይወጣ!” በማለት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ክፍል አንድ አንቀፅ 14ን በመነሻነት ጠቅሶ፤ ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሠሥ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት እንዳለው አስታውሷል።

መግለጫው አያይዞም የተለያዩ አንቀጾችን በመጥቀስ፤ ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብት እንዳለውና በሕግ በተደነገገ ከባድ ወንጀል ቅጣት ካልሆነ በቀር ሕይወቱን እንደማያጣ መደንገጉን፤ ማንኛውም ዜጋ በመረጠው የአገሪቷ አካባቢ መኖር እንደሚችል፤ የግል ሀብት ባለቤትነት ስለመከበሩ፤ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ፣ በቋንቋ፣ በዘር፣ በቀለም፣ በብሔር፣ … አመለካከት ልዩነት እንዳይደረግ ሕገመንግሥቱ እንደሚደነግግ፤ ከዚህም ሌላ የአፍሪካ ግለሰቦችና ሕዝብ መብቶች ስለመከበር የወጡትንም ውሳኔዎች አንስቶ መንግሥት እነዚህን የማስከበር ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ መግለጫው ይጠቅሳል።

ለዚህም ማጣቀሻ የሚኾኑ በቅደም ተከተል በአገሪቱ የደረሱን ጉዳቶች ዘርዝሯል። አሁንም ባለፈው ከማክሰኞ ጥቅምት 11 እስከ 13 ቀን 20112 ዓ.ም. በነተሳው ብጥብጥ ከ67 በላይ ሰዎች በተለያዩ አካባቢዎች ስለመሞታቸውና የአካል ጉዳተኞችም ስለመኖራቸው በዋንኛነት በመግለጫው ወቀሳውን አቅርቧል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ከሚፈጠሩ ሁከቶች ጋር ተያይዞ ብሔርንና እምነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግጭቶች በዜጎች ላይ ሲፈጸም፤ የዞንና የወረዳ አስተዳደር አመራሮች፣ የጸጥታ አካላት በሕግ የተጣለባቸውን ለዜጎች ጥበቃ የማድረግ ግዴታ ባለመወጣታቸውና በፍጥነት ድርጊቶቹን ባለመቆጣጠራቸው ችግሩ በከፍተኛ መጠን ተባብሶ ወደ ከፍተኛ ቀውስ እያመራ መገኘቱን ይኸው መግለጫ የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጧል።

ባላፉት ሁለት ዓመታት ዜጎች ንጹሕና ክቡር ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ አካለ ጎዶሎ ሲኾኑ፣ በመቶ ሺሕዎችች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ፣ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲዳረጉ፣ .. መንግሥት በዝምታ መመልከቱን ኢሰመጉ ኮንኗል።

መንግሥት ሕጋዊና የማያወላውል እርምጃ በመውሰድ የዜጐችን በሕይወት የመኖር፣ አካላዊ ደኅንነትና በፈለጉት የአገሪቱ አካባቢዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸውን እንዲያከብርና እንዲያስከብር ኢሰመጉ አሳስቧል። በተጨማሪም መንግሥት ማድረግ ስላለበት የኃላፊነት ድርሻ ዝርዝር አመላክቷል።

የሐሰት መረጃ የሚያሰራጩና ሕዝብን ወደብጥብጥ የሚከቱ የሚዲያ አውታሮችም ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በመግለጫው ማጠናቀቂያ ላይ አሳስቧል። የኢሰመጉን ሙሉ መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ