Chaltu Sanni and Addisu Arega

ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒና አቶ አዲሱ አረጋ

አዲሱ አረጋ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ተሹመዋል

ኢዛ (ዓርብ ኅዳር ፲፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. November 29, 2019)፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለስድስት ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ሹመት የሠጠ ሲሆን፣ አቶ አዲሱ አረጋና ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ኾነዋል።

የክልሉ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፤ አቶ ካሳሁን ጎፌ የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊ፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የድርጅት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ ሳዳት ነሻ በድርጅት ጽ/ቤት የከተማ ፖለቲካ ዘርፍ አደረጃጀት ኃላፊና አቶ አበራ ወርቁ በድርጅት ጽ/ቤት የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ኃላፊ በመኾን ተሹመዋል።

ዛሬ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ኾነው የተሾሙት ወይዘሮ ጫልቱ የተተኩት፤ ትናንት ወደ ብረታ ብረትና ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን ተዛውረው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኾነው በሹመት በሔዱት በአቶ አሕመድ ቱሳ ምትክ ነው።

በምክትል ርዕስ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ኾነው የተሰየሙት አቶ አዲሱ አረጋ፤ በኦዴፓ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ ከፍተኛ እንደኾነ ከሚታመንባቸው አባላት አንዱ እንደኮኑ ይነገርላቸዋል።

አቶ አዲሱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሠሩ ሲሆን፣ የኦሕዴድ የድርጅት ጉዳዮች ኃላፊ፣ የኦሮሚያ ክልል የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የኦዴፓ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ኃላፊ በመኾን መሥራታቸው ይጠቀሳል።

ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ዛሬ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ኾነው ከመሾማቸው ቀደም ብሎ፤ የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በመኾን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

በዛሬው ሹመት የኦሮሚያ ገቢዎች ባለሥልጣን በመኾን የተሾሙት አቶ ካሳሁን ጎፌ የወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን ቦታ መረከባቸውን ያመለክታል። ነባር የኦዴፓ አባል የኾኑት አቶ ካሳሁን በፌዴራል ደረጃ፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ደግሞ ከዚህ ቀደም የኦሮሚያ የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ በኢሕአዴግ ጽ/ቤት የፖለቲካና ሲቪክ ጉዳዮች ኃላፊ፣ በመኾን ማገልገላቸው ይጠቀሳል።

አቶ ሳዳት ነሻ የኦሮሚያ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ እንደነበሩ ይታወሳል።

የዛሬው ሹመት አሠጣጥና ትናንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በፊዴራል ደረጃ የተሠጡት ሹመቶች ተያያዥነት ያላቸው መስሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ