ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ከኖቤል ሽልማቱ መልስ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ሲያደርጉላቸው፣ ሐሙስ ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.፣ እ.ኤ.አ. December 12, 2019

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ከኖቤል ሽልማቱ መልስ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ሲያደርጉላቸው፣ ሐሙስ ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.፣ እ.ኤ.አ. December 12, 2019

“በሽልማቱ መልካም እድል ይዞ የመጣ ነው” ዶ/ር ዐቢይ

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 12, 2019)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሰላም ኖቤል ሽልማታቸውን ተቀብለው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ደማቅ አቀባበል ተደርጐላቸዋል። ሽልማቱ መልካም እድል ይዞ እንደሚመጣም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ አዲስ አበባ ሲገቡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ የሕብረተሰቡ ተወካዮች በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ለክብራቸው 21 ጊዜ መድፍ በመተኮስ የተጀመረው አቀባበል እስከ ቤተመንግሥት ድረስ ደስታቸውን በገለጹላቸው የአዲስ አበባና አካባቢዎችዋ ነዋሪዎች ታጅበው ነበር። ከአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎች በፈረስ በመኾን እስከ ቦሌ ቤተመንግሥት ድረስ በመጓዝ አቀባበሉን አሳምረውታል።

የኖቤል ሎሬት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ማለዳ ላይ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ እንደደረሱ በሠጡት አጭር መግለጫ፤ የኖቤል ሽልማቱ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም የሚያስተዋውቅና መልካም እድል ይዞ የሚመጣ መኾኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መግለጫቸው፤ ሽልማቱ ኢትዮጵያን ያስተዋወቀ መልካም እድልን ይዞ የሚመጣ ከመኾኑም በላይ በመስማማትና በመደማመጥ በአገር ፍቅር አገራችንን ለማሳደግ ይህንን መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ሽልማቱ ከኢትዮጵያ አልፎ ኤርትራና ምሥራቅ አፍሪካ በዓለም ደረጃ ትኩረት እንዲያገኙ፣ ስማቸውም በመልካም እንዲነሳ ያስቻለ መኾኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም “ሁሉንም በመወከል ሽልማቱን እኔ ብቀበልም፤ ሽልማቱ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ፣ ለፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂና ለእኔ እንዲሁም ለተቀሩት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ወዳጆች ሁሉ የተሠጠ በመኾኑ እንደ መልካም እድል በመጠቀም፤ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት እንደ መነሻ አድርጐ መጠቀም መልካም ይሆናል” በማለት አጋጣሚው የመልካም እድሎች መንደርደሪያ ማድረግ የሚገባ እንደሆነም አመልክተዋል።

የዚህን ሽልማት ደስታ ከአቶ ኢሳይያስ ጋር በጋራ በቅርቡ እንደሚያከብሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

በኖቤል ሽልማት ፕሮግራሙ ስለኢትዮጵያ ብዙ መባሉን በመግለጽ፤ ደሃ ብንሆንም ታሪክ ያለንና ለሠላም የምንተጋ ሕዝቦች መኾናችንን እንዲሁም ከዚህ ቀደም ያልተነሡ ታሪኮቻችንን እንዲወሱ እድል የተገኘበት መድረክ እንደነበር የጠቀሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ ለኢትዮጵያውያን የማስተላልፈው መልእክት በማለት የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል።

ከዘመናት በፊት የሌሎች አገራትን ሕዝቦች ተቀብላ ስታስተናግድ የነበረች አገር አሁን ታሪኳ እየቀጨጨና እየተረሳ የመጣ ቢሆንም፤ አሁንም የሚታደስበት እድል በመገኘቱ በተባበረ ክንድና በተስማማ ማንነት አገራችንን ካለችበት ሁኔታ ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር በጋራ ጠዋት ማታ እንድንተጋና እንድንጠቀምበት አደራ ማለት እፈልጋለሁ!። የኖቤል ሎሬት ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

ዛሬ በአዲስ አበባ የተደረገው አቀባበል ከቦሌ እስከ ቤተመንግሥት የተወሰነ አልነበረም። በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ነዋሪው ደስታውን በተለያዩ መንገዶች የገለጸ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ውጭም ሕዝቡ ደስታዊ ሲገለጽ ነበር። በጅማ ሕዝብ አደባባይ ወጥቶ እንኳን ደስ ያለን መልእክቱን ሲያስተላልፍ፣ በሐዋሳ በወላይታና በሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ ፕሮግራሞች ተካሒደዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተደረገላቸው ላለው አቀባበል ከሰዓት በኋላ በፌስ ቡክ ገጻቸው ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህም መልእክታቸው “ዓለም አገሬን ሲያከብሯት ዓይቼ ወደ አገሬ በመመለሴ ደስ ብሎኛል። የጋራ ድላችንን ለማክበር እጅግ ደስ የሚያስብል ላዘጋጃችሁልኝ ሁሉ ምስጋናዬ ይድረስ። ስንተባበር ሁሉ ይቻላል። በአብሮነት ሕልማችንን እውን እናደርጋለን።” በማለት ነበር።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ምሽት ላይ በታላቁ ቤተመንግሥት የምስጋና የራት ግብዣ የሚያደርጉላቸው ሲሆን፣ በፕሮግራሙ ላይ ዲፕሎማቶች፣ ባለሥልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ። (ኢዛ)

የአቀባበል ሥነሥርዓቱ በፎቶ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ