Prof. Berhanu Nega

የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

“ጉልበት የፋራ ነው” አሉ

ኢዛ (ሰኞ ታኅሣሥ ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 16, 2019)፦ የፖለቲካ ሥልጣን እናገኛለን ብለን ይቺን አገር ችግር ውስጥ ለመክተት እንደማይሠሩ የኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ። የጉልበት ፖለቲካ “የፋራ ነው” አሉ።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ይህንን የገለጹት ታኅሣሥ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ለፓርቲው ድጋፍ ለማሰባሰብ በተደረገው የራት ፕሮግራም ላይ ነው። ከኢትዮጵያ ሌላ አገር የሌለን በመኾኑ ለዚህች አገር በጋራ መሥራት አስፈላጊነትን ያጐሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በመመካከርና በመግባባት አገርን ወደፊት እንዴት እንወስዳለን በሚል በጋራ የሚሠራበት ጊዜ ላይ ነንም ብለዋል።

ነገር ግን ለፖለቲካ ሥልጣን ብለው ይቺን አገር በምንም መልኩ ችግር ውስጥ የማይከቱ መኾኑን በማስገንዘብ፤ ለሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች መንገር የሚፈልጉት ይህንኑ አመለካከት መኾኑን ገልጸዋል።

የፖለቲካ ድርጅቶችን፤ ሐሳባችሁን ገበያ ላይ አውጥታችሁ ተከራከሩም ብለዋቸዋል። ሐሳባችሁን ሕብረተሰቡ ከተቀበላችሁ ግን ብንወደው እንኳን እንቀበለዋለን በማለት የአገሪቱ ፖለቲካ ሐሳብን በመሸጥ ብቻ ፖለቲካን ማራመድ ይበጃል የሚል እምነታቸውን አንጸባርቀዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሐሳብን በማቅረብ በሚያደርጉት ፉክክር ሕዝብ የሚቀበለውን ፓርቲያቸው የሚቀበል ሲሆን፣ ሌሎች ፓርቲዎችም ይህንኑ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ሳይገልጹ አላለፉም።

ይህንንም ሐሳባቸውን ሲቋጩ “ከአሁን በኋላ በጉልበት የሚኾን ነገር የለም። ጉልበት ከአሁን በኋላ የፋራ ነው” በማለት ነው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር ላይ የሰነዘሩዋቸውን ቀሪውን ሐሳባቸውንና በሌሎች ጉዳይ የተገበሩትን የተቀረው ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ወደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ልንሻገር የምንችልበት አዲስ መስመር የምናሰምርበት ጊዜ ነው

ይሄ ጊዜ ቀላል ጊዜ አይደለም። እንዲህ ያለ ፋይዳ ያለው ነገር በቀላል ይገኛል ብላችሁ አታስቡ። ብዙ ትግል ይጠይቃል። ብዙ ሙከራ ይጠይቃል ብዙ ከፍና ዝቆች ይጠይቃል።

ተስፋ የምናደርገው ግን እነዚህን ትግሎች በጦርነት ሳይሆን በቃላት በሐሳብ በፖሊሲ እኛ ይህንን ነው የምናደርገው ብለን ከእኛ የተሻለ ይህን ነው የማደርገው የሚል ሲመጣ እሱ የሚያሸንፍበት፤ እኛም እሰየው ጥሩ ፖሊሲ አምጥተሃል እኛም በሚቀጥለው ጊዜ የሠራኸውን ዓይተን እኛም አሻሽለን እንቀርባለን የምንልበት፤ ፖለቲካ መጋደያና መታሰሪያ ሳይሆን የጋራ አገራችንን እንዴት እንገንባ ብለን የምንወያይበት ፖለቲካ ማድረግ ነው።

ይሄ ነው ለእኛ የቀረበልን የዘመኑ ጥያቄ ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ይህንን ጥያቄ ባለፈው ፍርሃት አሁንም ይህንን ጉዳይ ከዳር ኾነው እንደማይመለከቱም ጠቅሰዋል።

እርሳቸው የሚመሩት ፓርቲ አባላት የሚለዩት ዳር ኾነው እስኪ እንመልከት ከሚሉት ጐራ ያለመሆናቸውን በማስታወስ፤ እንደማንም ሰው በአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ማለት እንደሚገባ ተናግረዋል።

“ከአሁን በኋላ የኔ ብለን የምንሔድበት ሌላ አገር የለም።” በማለትም ከዚህ በኋላ ይሄ አገር አያስተማምንም ብሎ ውጭ ለመሔድም የማይቻልበት ወቅት እንደሆነ አስታውሰዋል። ምክያታቸው ደግሞ ዓለም በሙሉ ስደተኛ የሚባል ነገር በፍጹም ትግስት የሌለው ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው። ስለዚህ ያለችን አገር ይቺ አገር በመኾንዋ፤ ይቺን አገር በጋራ በስምምነት እንዴት አድርገን ወደፊት እንወስዳለን ብለን በጋራ የምንመክርበት ጊዜም ነው ብለዋል።

ጦርነት የጀግንነት ምልክት መኾኑ እንዳበቃ ያወሱት የኢዜማ መሪ፤ “አሁን ጀግንነት ሠላም ማምጣት ነው። አሁን ጀግንነት አገርን በጥሩ ማስተዳደር ነው” ብለዋል። ዶክተር ዐቢይ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የኾነው ኮሎኔል ስለሆነና ስለተዋጋ ያለመኾኑንና በተቃራኒው ሰላም ስላመጣና ለሰላም እንደሚታገል ስላሳየ መኾኑን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ