Birtukan Mideksa

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ)

ሕትመቱ ከኢትዮጵያ ውጭ ሲደረግ የመጀመሪያው ነው

ኢዛ (ሐሙስ ታኅሣሥ ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. December 19, 2019)፦ ቀጣዩን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካሔድ ይረዳሉ የተባሉ የሕትመት ሥራዎችን ከኢትዮጵያ ውጭ ለማሳተም ስምምነት መፈረሙን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ የሚኾኑ የመራጮች ምዝገባን ዘመናዊና ተአማኒነትን የሚያረጋግጥ የሕትመት ሥራ ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት መፈረሙን ያስተወቀው ትናንት ታኅሣሥ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው። የምርጫ ሒደቱ ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እንዲኾን አጋዥ ይሆናሉ የተባሉት የሕትመት ሥራዎችን ለመሥራት ስምምነት የተፈረመው በዱባይ ነው። አዲሱ የምርጫ ሕግ ላይ የተቀመጡትን መሥፈርቶች ሊያሟላ በሚችል መልኩ ይታተማሉ የተባሉት የመራጮች ምዝገባ የሕትመት ውጤቶች፤ በምርጫው ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ ስሕተቶችን ለመቀነስና ማጭበርበርን ለማስወገድ የሚረዳ እንዲኾን፤ እንዲሁም ለምርጫ አስፈጻሚዎች ለመረዳትና ለማስፈጸም ቀላል እንዲኾን ለማድረግ እንደኾነም ተገልጿል።

ይህ የሕትመት ሥራ ከዚህ በፊት ከነበሩትና አገር ውስጥ ከሚደረጉ ሕትመቶች የተለየ ሕትመት ስለመኾኑም የምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የመራጮች መመዝገቢያ መዝገቡም ኾነ የምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ የራሳቸው የደኅንነት ማረጋገጫ ያላቸውና ሊጭበረበሩና ሊባዙ የማይችሉ መኾናቸው፤ የመራጮች ካርድ ቀሪ ያለው ኾኖ የሚዘጋጅና መራጮች ጋር ያለው ካርድ ቀሪ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር የሚቀር መኾኑ በምዝገባ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ማጭበርበርን የሚያስቀር ነው ተብሏል። እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች ካርዱ አማካኝነት የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር ያለው ሲሆን፣ ሁሉም ሰነዶች በአምስት ቋንቋዎች የሚታተሙ ናቸው። ሕትመቱ በአማርኛ፣ በአማርኛ/ትግርኛ፣ በአማርኛ/አፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ/ሶማሊኛ እንዲሁም በአማርኛ/አፋርኛ የሚታተሙ ስለመኾናቸውም መረጃው ያሳያል።

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ለማከናወን ሌሎች አስፈላጊ ዝግጅቶችን እያደረገ መኾኑንም አስታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ