አብን የሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ጊዜው አሁን ነው አለ
አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ)
ጊዜያዊ መንግሥት እንዲመሠረትም ጥሪ አቅርቧል
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 29, 2020)፦ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጊዜው አሁን መኾኑንና ብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋም እንደሚገባ ጥሪ ያስተላለፈበትን መግለጫ ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. አውጥቷል።
“በአዲስ ማኅበራዊ ውል የምንደራደርበትና የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የማሻሻያው ጊዜ አሁን ነው” በሚል ርዕስ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ይመለከታቸዋል ላላቸው ተቋማት በስማቸው እንዲደርሳቸው ባደረገው በዛሬው አቋሙ፤ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የቀረበ ታሪካዊ አገራዊ ጥሪ መኾኑንም አስታውቋል።
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መራዘሙን በማስታወስ የሚጀምረው የአብን የዛሬው መግለጫ፤ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም የሥልጣን ዘመኑ የሚጠናቀቅ በመኾኑ፤ በሕገ መንግሥቱም ኾነ በሌሎች የአገሪቱ ሕጎች ምርጫውን ለማራዘም የሚቻልበት ድንጋጌ እንደሌለም አክሏል።
ስለኾነም ሁኔታው ብሔራዊ የአንድነትና ጊዜያዊ መንግሥት የማቋቋም፤ እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት አዲስ ማኅበራዊ ውል የምንገባበትን ጊዜ አስፈላጊ እንዳደረገው ንቅናቄው ያምናል ብሏል።
ስለዚህ መንግሥት ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም የሕገመንግሥት ማሻሻያ ሒደት እንዲጀመር አብን ጥሪ የሚያቀርብ መኾኑንና ለዚህም ስኬት ሁሌም ኢትዮጵያውያን ከጎኑ እንዲቆሙ ጠይቋል።
በዚሁ በዛሬው መልእክቱ እንዲሻሻሉ የሚፈልጋቸውን የሕገመንግሥቱን አንቀጾችን ጭምር በመጥቀስ፤ ሰፋ ያለ ማብራሪያ አካትቷል።
አንቀጽ 39ን በተመለከተ፤ “መገንጠል መሠረታዊ የኾነው የፌደራሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ማለትም የድርድር ጉዳይን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ተግዳሮት ነው፡፡ መገንጠል ከፌደራሊዝም ጋር አብሮ የሚሔድ አይደለም፤ መገንጠል ያልሠለጠነ ድርድርን ይጋርጣል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሊሰጠው ይገባል፤ ነገር ግን የመገንጠል መብት ሊሰጠው አይገባም። ይህ የመገንጠል ጽንሰ ሐሳብ ያለምንም ሁኔታዎች (Conditions) በሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ማካተት የአገሪቱን ሉዓላዊ አንድነት ለአደጋ ማጋለጥ ነው።” በማለት ማሻሻይ እንዲደረግበት ጠይቋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ዛሬ ከወቅታዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ አቁሙን ያንጸባረቀበትን ደብዳቤ ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)



