ወይዘሮ አዳነች የመጀመሪያዋ ሴት ዓቃቤ ሕግ ኾኑ
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ, ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሒና አቶ ላቀው አያሌው (ከግራ ወደቀኝ)
የአራት ሚኒስትሮች ሹመት ጸደቀ፤ ሕወሓት ተቃወመ
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 12, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሃያ አንድ የሕወሓት ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ያሠሙበትን የአራት ሚኒስትሮች ሹመት በአብላጭ ድምፅ አጸደቀ።
ዛሬ ሹመታቸው ከጸደቀው አራቱ ሚኒስትሮች ውስጥ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከገቢዎች ሚኒስትርነታቸው ለቀው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኾነዋል። ይኸውም የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መኾን አስችሏቸዋል።
ቀሪዎቹ ሦስቱ አዳዲስ ሹመቶች ትናንት እንደተተነበየው ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር፤ አቶ ላቀ አያሌው ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ተክተው የገቢዎች ሚኒስትር፤ ወ/ሮ ፊልሰን አብዱላሒ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ኾነው ተሹመዋል።
በዚህ ሹመት የማጽደቅ ሒደት ላይ የሕወሓት የምክር ቤት አባላት ሹመቱን በመቃወም ድምፅ የሠጡ ሲሆን፣ የሹመት አሠጣጡ የትግራይ ተወላጆችን ያገለለ ነው እስከማለት ደርሰዋል። እንዲህ ላለው አስተየየት ሌሎች የምክር ቤት አባላትም አስተያየቱ ትክክል ያለመኾኑን በመግለጽ፤ ከሕወሓቶች የቀረበውን አስተያየት ውድቅ አድርገውታል።
በዕለቱ በሚኒስትርነት ከተሾሙት ውስጥ አቶ ላቀው አያሌው የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩ መኾኑ ይታወሳል።
ዶ/ር ሊያ ታደሰም የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል። የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር በመኾን የተሾሙት ወ/ር ፊልሰን፤ “ነበድ” የተባለ በሱማልኛ ቋንቋ የሚተላለፍ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያ መሥራችና ሥራ አስፈፃሚ ናቸው።
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት የፌዴራሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አድርጎ አቶ ጸጋ አራጊን የሾመ ሲሆን፣ በነበረው የድምፅ አሠጣጥ በ11 ተቃውሞ፣ በ6 ድምፀ ተአቅቦና በአብላጫ ድምፅ ሹመቱ መጽደቁ ታውቋል። (ኢዛ)



