የአገሪቱ ትልቁ ባንክ ከነገ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ይዘጋል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መደበኛ ሥራውን የሚጀምረው የፊታችን ሰኞ ነው
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 8, 2020)፦ የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የኾነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከነገ ሚያዝያ 1 ቀን ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀኖች አገልግሎት እንደማይሠጥ አስታውቋል። ባንኩ መደበኛ ሥራውን የሚጀምረው ሰኞ ሚያዝያ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው።
ከነገ ሚያዝያ 1 ቀን እስከ ሚያዝያ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ባንኩ በሁሉም ቅርንጫፎች አገልግሎት የማይሠጠው የቴክኖሎጂ አቅም ማስፋፊያ ሥራውን ተግባራዊ ለማድረግ መኾኑን አስታውቋል።
እንደባንኩ መረጃ በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች መደበኛ የባንክ አገልግሎቶች ባይሠጡም በኤቲኤም ማሽኖቹ ገንዘብ ማውጣት የሚቻል መኾኑን ገልጿል።
ከዚህም ሌላ ፖስ እና ሲቢኢ ብር የባንኩ አገልግሎት ዝግ በሚኾኑባቸው ቀናት አገልግሎት ይሠጣሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአገሪቱ ውስጥ ካሉ 18 ባንኮች ከፍተኛ የደንበኞቹ ቁጥር ያሉት እንደኾነ ይጠቀሳል። በአሁኑ ወቅት የባንኩ አስቀማጮች ቁጥር (ዲፖዚተርስ) ከ23 ሚሊዮን በላይ ናቸው። ባንኩ በመላው አገሪቱ ያሉት ቅርንጫፎች ቁጥርም ከ1560 በላይ ናቸው። (ኢዛ)



