የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነገውን ስብሰባ በራሱ የስብሰባ አዳራሽ አያካሒድም

አዋጁ የሚጸድቀው ከፓርላማው ሕንፃ ውጭ ነው

ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 9, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውጭ በሚደረግ ልዩ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ነገ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት ዓርብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የሚያጸድቀው በአራት ኪሎ በሚገኘው የስብሰባ አዳራሹ እንደማይኾን እየተነገረ ነው።

በምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማጽደቅ ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አፈፃፀም መርማሪ ቦርድ አባላት ለመሰየም የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የነገውን ስብሰባ ከራሱ ሕንፃ ውጭ ለማድረግ የተገደደው በፓርላማው አዳራሽ ቦታ ተራርቆ ለመቀመጥ የማያስችል በመኾኑ ነው ተብሏል።

ለኮሮና ቫይረስ ሥርጭት አንዱ ርቀትን መጠበቅ በመኾኑ፤ በፓርላማው የሚታየው አቀማመጥ የተጠጋጋ በመኾኑ ይህንን ለማስቀረት ነው። ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ስብሰባው በትክክል የት እንደሚካሔድ በይፋ አልተገለጸም። በቤተመንግሥት ወይንም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊካሔድ ይችላል የሚሉ ግምቶች ቢኖሩም፤ በቤተመንግሥት ሊካሔድ እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ