Fitsum Arega, Ethiopian Ambassador to the United States

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ

በአብዛኛው እየሞተ ያለው አፍሪካ አሜሪካውያን በሚል ካታጎሪ የተመደቡ ናቸው

ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 17, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ በእጅጉ እየደቆሳት ባለችው አሜሪካ በተወሰነ ደረጃ ከተሰበሰቡ መረጃዎች 100 የሚኾኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተመለከተ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለቪኦኤ እንደገለጹት፤ እስካሁን ባላቸው መረጃ ከ100 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን በዚሁ ወረርሽኝ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

ይህ አኀዛዊ መረጃ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበራትና መሰል ተቋማት የተገኘ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከዚህም ሊልቅ የሚችል ስለመኾኑ የአምባሳደሩ ገለጻ አመላካች ኾኗል።

በአሜሪካ በቫይረሱ ተጠቅተው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ቁጥር በተመለከተ በሠጡት መረጃ፤ “የቁጥር መረጃዎችን ከእድር ሰዎች ጋር ግንኙነት አለኝ፤ በነሱ አማካኝነት የምናገኘው አለ። ግን የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ቁጥር ይቅርና የአፍሪካ አሜሪካኖች ቁጥር ለማውጣት ፖለቲካሊ ሴንስቲቭ ስለኾነባቸው መረጃውን በቀላሉ እያገኘን አይደለም” ብለዋል።

ነገር ግን በተለያዩ ማኅበራት በኩል ከሚያገኙት መረጃ፤ እንዲሁም በየስቴቶቹ ካሉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲዎችና ከመሳሰሉት ካገኙት መረጃ፤ ከ100 ያላነሱ ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያውያኑን ቁጥር በትክክል ለማግኘት ያልተቻለውና ነገሩ ፖለቲካሊ ሴንስቲቭ የኾነው፤ በአብዛኛው እየሞተ ያለው አፍሪካ አሜሪካውያን በሚል ካታጎሪ የተመደቡ በመኾናቸው፤ እዚህ ውስጥም ኢትዮጵያውያን እንዳሉበት መረዳታቸውንም ጠቅሰዋል።

በመላው ዓለም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት ከሚኖሩባቸው አገሮች መካከል አሜሪካ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሲሆን፤ በአሜሪካ ብቻ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይገመታል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ