በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አስጫሾችና አስቃሚዎች፤ እንዲሁም ዕቃዎቻቸውና ጫት

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ አስጫሾችና አስቃሚዎች፤ እንዲሁም ዕቃዎቻቸውና ጫት

ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ሲሻ ሲያስጨሱና ጫት ሲያስቅሙ የነበሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል

ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 23, 2020)፦ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በማፃረሩ ተግባራት ላይ ተሰማርተው በሚገኙ ግለሰቦች ላይ እርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑን ሰሞኑን በተከታታይ የሚወጡ መረጃዎች እያመላከቱ ነው። ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ ሲሻ ሲያስጨሱና ጫት ሲያስቅሙ የነበሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳመለከተው፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተከለከሉ ተግባራት ውስጥ ተሰብስቦ ጫት መቃምና ማስቃም አንዱ ነው። በዚህም መሠረት ዛሬ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍ 31 የሚኾኑ ግለሰቦች ተሰባስበው ጫት ሲቅሙ ተገኝተው በቁጥጥር ስር አውሏቸዋል።

በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማም አሜሪካ ግቢ በሚባለው አካባቢ ሸራ ወጥረው ሕገወጥ ቤት በመሥራት 20 ሰዎችን ሲሻ ሲያስጨስ የነበረ ግለሰብ፤ ከ30 በላይ ከሚኾኑ የሺሻ ማስጨሻ ዕቃዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋሉም ታውቋል።

በተመሳሳይ ዜና በዚሁ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጐማ ተራ አካባቢ በመኖሪያ ቤታቸው ሺያ ሲያስጨሱ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

በሁለቱ መኖሪያ ቤቶች 15 ሰዎች ሲሻ ሰያጨሱ መገኘታቸውና 66 የሺሻ ማጨሻዎች መያዛቸውንም ይጠቅሳል።

እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ የኾኑ እርምጃዎችን ፖሊስ እየወሰደ ሲሆን፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ሕክምና ከሚደረግበት ኮተቤ የካ ሆስፒታል ውስጥ ግላቭ የሰረቁ ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መኾኑን መገለጹ ይታወሳል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ ከትናንት በስቲያ ይፋ በተደረገ የፖሊስ መረጃ ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴን በተመለከተ የተደነገገውን ደንብ የተላለፉ አሽከርካሪዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል። እንደ ፖሊስ መረጃ ከመጋቢት 28 እስከ ሚያዚያ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. 195 አሽከርካሪዎች ከተፈቀደው በላይ ትርፍ ጭነው በመገኘታቸው፤ እንዲሁም 73 አሽከርካሪዎች ከትርፍ በላይ በማስከፈላቸው እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ዛሬ ከአማራ ክልል መገናኛ ብዙኀን እንደገለጸው ደግሞ በሰሜን ሸዋ ዞን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመተላለፍና ዞኑ እንዳይከፈቱ ተከልክለው እያለ የተከፈቱ 60 ጫት ቤቶች፣ 517 ፑል ቤቶች፣ እና 285 ሺሻ ቤቶች አሽጓል። ከዚህም ሌላ ለኮሮና ወረርሽኝ ምቹ እንደሚኾኑ የተለዩ 326 ቤቶች መታሸጋቸውን ይኸው መረጃ ይገልጻል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ