የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄውን በአጭር ጊዜ ለመመለስ እየተሠራ ነው ተባለ
የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ
አጣሪ ኮሚቴው በአሥር አባላት ሥራ ጀምሯል
ኢዛ (ሐሙስ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. May 14, 2020)፦ በቅርቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሠራ መኾኑን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢዋ አስታወቁ። በትርጓሜው ዙሪያ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በመኾን የሚደረገው ውይይት ለሕዝብ ይተላለፋል።
የአጣሪ ጉባዔው ሰብሳቢና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቁት፤ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄውን በአጭር ጊዜ ለመመለስ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ነው። በሕገ መንግሥት ጉዳዮች ትርጉም ጥያቄ ዙሪያም፤ አሁን በሥራ ላይ ባሉ አሥር የጉባዔው አባላት ሥራ ስለመጀመሩም የወይዘሮ መዓዛ ማብራሪያ ያመለክታል።
እንደ ወይዘሮ መዓዛ ገለጻ፤ ለአጣሪ ኮሚቴው የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሚያስፈልገው መኾኑ ይመረመራል። ትርጓሜው የሚሰጠው ጥያቄ ከኾነውም የውሳኔ ሐሳቡ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲቀርብ ይደረጋል ብለዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ምርጫ 2012 እንዲራዘም መወሰኑ አይዘነጋም። ይህንኑ ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በቀጣይ የሚካሔደውን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የተቀመጡ ሦስት አንቀፆች በሕገመንግሥታዊ ትርጓሜ እንዲሰጣቸው ማጽደቁን ተከትሎ ነው ይህ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የተሰየመው። (ኢዛ)



