ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ በአምነስቲ መግለጫ ላይ ተናገሩ
አምነስቲ ኢንተርናሽናል
ዓለም እውነቱን እንዲያውቅ እናደርጋለን ብለዋል
ኢዛ (ማክሰኞ ግንቦት ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 2, 2020)፦ ሰሞኑን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን መግለጫ ተከትሎ የተለያዩ ተቃውሞዎች እየቀረቡ ሲሆን፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥት አቋም የሚያንጸባርቅ መልእክት አስተላልፈዋል።
ወይዘሮ አዳነች በመረጃ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፤ ሰብዓዊ መብት የምናከብረውና የምናስከብረው ለማንም ብለን ሳይሆን ለሕዝባችንና ለፍትሕ ስንል ነው ብለዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የወጣውን መግለጫ መመልከታቸውንና የማጣራት ሥራ መጀመራቸውን የገለጹት ወይዘሮ አዳነች፤ “የማጣራት ሥራችንን አጠናቀን ምላሽ ለመስጠት በሒደት ላይ እያለን መግለጫው በተለያዩ ሚዲያዎች ተሠራጭቷል” ብለዋል።
አያይዘውም አሁንም ቢሆን ዘገባውን ከይዘቱ፣ ከአካሔዱ፣ እንዲሁም የጉዳዩን እውነተኝነትና ገለልተኝነት የማጣራት ሥራዎችን በቶሎ ለማጠናቀቅ እየሠሩ መኾኑንም ገልጸዋል። በማጣራት ሥራው የሚገኘውን ውጤት፣ ሪፖርት እውነት በኾነበት ልክ መወሰድ ያለበትን እርምጃ እንደሚወስዱና ሐሰት በኾነበት፤ ወይም በተጋነነበት አኳያ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋር በመወያየት ሪፖርቱ እንዲስተካከል ጥረት የሚያደርጉ መኾናቸውንም በዚሁ መልእክታቸው ጠቅሰዋል።
ይህ ባይቻል እንኳን ሕዝባችንና ዓለም እውነቱን እንዲያውቅ በመረጃ አስደግፈን እናሳያለን በማለት መልእክታቸውን ቋጭተዋል።
አምነስቲ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፤ በዋናነት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተፈጸሙ ያላቸውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ያመላከተበት ነበር። ኾኖም ይህ መግለጫ ፍጹም ሚዛናዊነት የጐደለው ስለመኾኑ የተለያዩ ወገኖች እየገለጹ ይገኛሉ። (ኢዛ)



