አቶ ለማ መገርሳ ከመከላከያ ሚኒስትርነታቸው ተነሱ
አቶ ለማ መገርሳ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሹምሽር አካሔዱ
ኢዛ (ማክሰኞ ነኀሴ ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 18, 2020)፦ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለአሥር ሰዎች ሹመት መስጠታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ኢንጂንየር ታከለ ኡማ ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነት ተነስተው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኾነው ተሹመዋል።
አቶ ለማ መገርሳ ከሥልጣናቸው ተነስተው ዶ/ር ቀንዓ ያደታ የመከላከያ ሚኒስትር ኾነው ሲሾሙ፤ በወ/ሮ አዳነች አቤቤ ምትክ ደግሞ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ኾነው ተሹመዋል።
ፕሮፌሰር ሒሩት ወልደማርያም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትርነታቸው ተነስተው በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ ኾነው ሲሾሙ፤ በምትካቸው ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ኾነዋል።
ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኾነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን፤ በምትካቸው የአዲስ አበባ ከትማ ምክትል ከንቲባ የነበሩት ኢንጂንየር ታከለ ኡማ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትርነቱ ሹመት ተቀብለዋል።
አቶ ተስፋዬ ዳባ እና አቶ ፍቃዱ ጸጋ የፌዴራሉ ምክትል ዓቃቤ ሕግ ኾነው የተሾሙ ሲሆን፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የነበሩት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ደግሞ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኾነው ተሹመዋል። አቶ ፍቃዱ ጸጋ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
በያዝነው ዓመት የካቲት ወር መጀመሪያ ድረስ በአማራ ክልል በምክትል መስተዳድር ማዕረግ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትና ከክልሉ ተነስተው ወደ ፌዴራል መንግሥቱ ለአዲስ ሹመት ይታጫሉ ተብሎ፤ “የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ” ፕሬዝዳንትነት ሹመት ተሰጥቷቸው፤ ሹመቱን አልቀበልም ብለው የነበሩት አቶ ዮሐንስ ቧያለው በዛሬው ዕለት አዲስ ሹመት ከተሰጣቸው ውስጥ አንዱ ናቸው። በዚህም መሠረተ አቶ ዮሐንስ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኾነው ተሹመዋል።
አሥረኛው ተሿሚ ኢንጂንየር እንዳወቅ አብቴ ሲሆኑ፤ የብረታ ብረት ኢንጂንየሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኾነው ተሹመዋል። ኢንጂንየር እንዳወቅ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ተቋማት አስተባባሪ ኾነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። (ኢዛ)



