Ato Lidetu Ayalew

አቶ ልደቱ አያሌው

“ፍርድ ቤቱ የአንድ ወገን ብቻ እየሰማ ነው” አቶ ልደቱ

ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 24, 2020)፦ ለአራተኛ ጊዜ በቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ ተደረገ።

አቶ ልደቱ ለእስር የተዳረጉት የአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ሰኔ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. አመጽና ኹከት እንዲነሳ ወጣቶችን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል ተጠርጥረው እንደኾነ አይዘነጋም።

በዛሬው ዕለት (ሰኞ ነኀሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም.) በዋለው ችሎት አቶ ልደቱ በጠበቃቸው በኩል፤ ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ ታስረው በዓቃቤ ሕግ በኩል ማስረጃ መቅረብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤት ነፃ እንዳደረጋቸውና ለፍርድ ቤት ክብር እንዳላቸው በመግለጽ፤ በዚህኛው ክስ ለከሳሻቸው በተደጋጋሚ ጊዜ እየተሰጠ መኾኑንና ይህም ተገቢ አለመኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህም በተጨማሪ “የሕክምና ማስረጃ አቅርቤ ለሕክምና ዋስትና ስጠይቅ ውድቅ መደረጉ፤ የአንድ ወገን ብቻ እየተሰማ መኾኑን ያሳያል። አራት ጊዜ ዳኞች እየተቀያየራችሁ ነው፤ መርማሪ ፖሊስም ተደጋጋሚ አንድ ዐይነት ምርመራ እያቀረበ ነው ያለው” በማለት ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል።

ዓቃቤ ሕግ በበኩሉ አቶ ልደቱ በአገር ውስጥ ሕክምና ማግኘት የሚችሉ መኾኑን ጠቅሶ፤ ወደ ውጭ ቢወጡ በዚያው ይቀራሉ በማለት መከራከሪያ በማቅረብ የዋስትና ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሊያገኝ አይገባም ብሏል።

ከዚህም ሌላ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው ዓቃቤ ሕግ፤ ተጨማሪ የ14 ቀን የጠየቀውም አቶ ልደቱ እጅ ላይ የተገኘው የሽግግር መንግሥት መመስረቻ ሰነዶች፣ የስልክ ልውውጥና ሲዲ ለምርመራ በመላኩ፤ እንዲሁም አጠቃላይ የምስክር ቃል ለመቀበልና የዚህን ምርመራ ውጤት ለማጣራት መኾኑን ገልጿል።

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም፤ የአቶ ልደቱን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ፤ ዓቃቤ ሕግ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በግማሽ ቀንሶ ሰባት ቀን ፈቅዷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ ይቀረኛል የሚለውን የምርመራ ውጤት አጠናቅቆ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ