አሥር የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች

አሥር የአማራና የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች

ተስማምተውበታል በተባሉት አሥር ነጥቦች ፊርማቸውን አስቀምጠዋል

ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 23, 2020)፦ አሥር የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የፖለቲካ አቋሞች ላይ ስምምነት በመድረስ መፈራረማቸው ተገለጸ።

እነዚህ አሥር ፓርቲዎች ለአሥር ወራት ሲወያዩ ቆይተው ተስማምተውበታል በተባሉት አሥር ነጥቦች ፊርማቸውን ስለማኖራቸው፣ ከፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በኋላ የተሰራጨው መረጃ ያስረዳል።

እነዚህ አሥር ፓርቲዎች ዛሬ ስምምነት ላይ ደርሰውበታል የተባለው አሥር ነጥብ በዝርዝር ቀርቧል። የውይይታቸው መነሻ ባለፈው ዓመት በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግጭት ነው ተብሏል።

በዚህ ግጭት ጀርባ የፖለቲካ ተዋንያን አሉ በሚል ግንዛቤ፤ ሁኔታውን ለማርገብ እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች ገለልተኛ ሰዎች ተመርጠው ሲወያዩ እንደነበርና ለዛሬው ስምምነት ስለመደርሱ ተጠቅሷል።

ባለፈው ዓመት ይህ የውይይት መድረክ እንዲጀመር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ናቸው።

በዛሬው ስምምነት ላይ ፊርማቸውን ካሰፈርት የፖለቲካ ፓርቲዎች አምስቱ ከአማራ፣ አራቱ ደግሞ ከኦሮሞ ሲሆኑ፤ አሥረኛው ፓርቲ ብልጽግና ፓርቲ ናቸው። የአማራ ብልጽግና እና የኦሮሞ ብልጽግና በዚህ ስምምነት ላይ የተካተቱ ሲሆን፤ ብልጽግና እንደ አንድ ፓርቲ ከተቆጠረ ስምምነቱን የፈረሙት አሥር ፓርቲዎች ይኾናሉ።

እነዚህም ፓርቲዎች ብልጽግና (የአማራና የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የአማራ ሕልውና ለኢትዮጵያ ድርጅት፣ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ፣ የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ፣ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት፣ ነጸብራቅ አማራ ድርጅት፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ውህደት እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ ናቸው።

ፓርቲዎቹ የተስማሙባቸው አሥር ነጥቦች የሚከተሉት ናቸው፤

1. የአገራችንን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች የኾነ ቀጣይ አገራዊ ውይይትና ድርድር ማካሔድ፤

2. ጥርጣሬ፣ መከፋፈል፣ እርስ በእርስ መቃረን፣ ወደ ዳር መገፋፋት፣ አንዱ የሌላውን ስም ከማጥፋት እንዲሁም ሕዝብ ለሕዝብ ከሚያጋጩና ከሚያቃቅሩ ድርጊቶች መቆጠብ፤

3. አገራዊ የሕዝብ ቆጠራ ተዓማኒነትና ተቀባይነት ባለው አሠራር በማካሔድ የሁሉም የአገሪቱ ብሔርና ብሔረሰቦች የሕዝብ ብዛት በአግባቡ ተቆጥሮ እንዲታወቅ ማድረግ፤ የከዚህ በፊቱ ግድፈቶች የሚያርምና የማይደገምበት መኾኑን ማረጋገጥ፤

4. በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት፣ የግልና የቡድን መብቶችን ማስከበርና በየጊዜውና በየደረጃው ነፃና ፍትሐዊ ምርጫን ማካሔድ፤

5. የኢትዮጵያ የታሪክ አቀራረብ የታሪክ አንጓዎችን ተከትሎ ከሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች በተውጣጡ የታሪክ ምሁርን የአገሪቱን ሕዝቦች ግንኙነትና ታሪክ ጥናት እንዲካሔድ፣ የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም እንዲቋቋም፤

6. በኦሮሞና በአማራ ክልሎች የሚኖሩ የሁሉም ሕዝቦች አባላት ደኅንነትና መብቶች እንዲከበሩ፤

7. በአገራችን በሁሉም አካባቢዎች ሰላምና ጸጥታ፣ ሕግና ፍትሕን ማስፈን፣ ከየቦታው ያለአግባብ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸውና ኑሮአቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ፤

8. አገሪቱ የምትተዳደርበት ሕገ መንግሥት ሁሉን አሳታፊ በኾነ መንገድ እንዲሻሻል ማድረግ፤

9. በአገሪቱ ዘላቂና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ልማት ማጎልበት፣ የሕዝቦቻችንን ፍትሐዊ የኢኮኖሚና የሀብት ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤

10. የተለያዩ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን የሚያጠናክሩ ዝግጅቶችን በጋራ ማዘጋጀት፤

ከላይ የተጠቀሱት የጋራ የፖለቲካ አቋሞች ላይ ፓርቲዎቹ መስማማታቸውንና በተቀሩ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ለመወያየትና ተመሳሳይ አቋም ለመያዝ ወደፊት ተመሳሳይ ውይይቶች እንደሚያካሒዱ ተገልጿል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ