በመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ለሦስት ወር እንደሚቀጥል ተገለጸ

ቤንሻንጉል ጉሙዝ
ኮማንድ ፖስቱ በመከላከያ ሠራዊት በበላይነት ይመራል
ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 24, 2020)፦ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለአንድ ዓመት ቆይቶ የነበረው የኮማንድ ፖስት በመተከል ዞን ለሦስት ወሮች እንዲቀጥል ተወሰነ።
የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው የአካባቢውን ሰላም ለማጠናከር በክልሉ ፕሬዝዳንት የሚመራው ኮማንድ ፖስት ለቀጣዮቹ ሦስት ወሮች ይቀጥላል።
ይህ ኮማንድ ፖስት በዋነኝነት በቅርቡ በክልሉ ከተፈጠረ ጥቃት ጋር ተያይዞ ሰላም ለማስፈን የሚሠራ ሲሆን፤ ሥራውንም ከአጎራባች ክልሎችና የጸጥታ ኃይሎች ጋር ይሠራል ተብሏል።
ግጭት በተደጋጋሚ የተከሰተባቸው ወረዳዎች ላይ የኮማንድ ፖስቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴዎች በአገር መከላከያ ሠራዊት በበላይነት እንደሚመራ ተገልጿል።
በሚቀጥሉት ሦስት ወሮች የጦር መሣሪያዎች እና ማንኛውም ስለታማ ነገሮች ይዞ መንቀሳቀስ የማይቻል ሲሆን፤ ሌሎች ክልከላዎችም ተጥለዋል።
በሦስት ወር ውስጥ የኮማንድ ፖስቱ ዋነኛ ሥራ ይኾናል የተባለው በሰሞኑ ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ሙሉ ለሙሉ ወደ ቀዬአቸው በመመለስ በዘላቂነት ማደራጀት የሚል ይገኝበታል።
በሰሞኑ ጥቃት በቁጥጥር ሥር ያልዋሉትን አድኖ የመያዝ ሥራም የኮማንድ ፖስቱ ይኾናል ተብሏል።
ከነኀሴ 23 ቀን እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቤንሻንጉል ክልል በተፈጸመ ጥቃት ከ5,600 በላይ ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እንዳስታወቀው ደግሞ፤ በዚህ ጥቃት እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ከ370 በላይ ተይዘዋል። እስካሁን ይፋዊ መረጃ ባይኖርም በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በዚህ ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል። (ኢዛ)