ኢሬቻ፣ Irrecha

የኢሬቻ በዓል ሲከበር

ፖሊስ ባደረገው ክትትል 14 ክላሽ 26 የእጅ ቦንብና 103 ሽጉጦችን መያዙን ገለጸ
በዓሉን የሚከብሩት ከስድስት ሺህ የማይበልጡ ታዳሚዎች ናቸው

ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 2, 2020)፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ መስከረም 23 እና 24 ዓ.ም. የሚከበረው የኢሬቻ በዓል በሰላማዊ መንገድ እንዳይካሔድ ሲንቀሳቀሱ ነበር ያላቸውን ከ500 በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና የጦር መሣሪያዎችን መያዙን አስታወቀ።

የክልሉ ፖሊስ ሐሙስ መስከረም 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ስለማድረጉ ገልጾ፤ ኾኖም በዓሉን ለማወክ እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት መኖራቸው በመታወቁ፤ የክልሉ ፖሊስ በዓሉን ለማወክ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከ500 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር አውሏል።

በዓሉን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የዜጐችን ሕይወት አደጋ ላይ ለመጣልና ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማጋጨት የሚንቀሳቀሱ ስለመኖራቸው በማስረጃና በመረጃ ማግኘቱን የሚያመለክተው የክልሉ ፖሊስ መግለጫ፤ ከዚህ ድርጊት ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አመልክቷል።

ችግር የሚፈጥር ካለ እርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቂያ ያከለው መግለጫ፤ ለዚህም የክልሉ ፖሊስ ዝግጁ ስለመኾኑም ያመለክታል።

በሰላም እንዲከበር ኦሮሚያ ፖሊስ ካደረገው ዝግጅት ሌላ የአዲስ አበባ ፖሊስም በተመሳሳይ ዝግጅቱን ማጠናቀቁና የጸጥታ ጥበቃው ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በትብብር የሚሠራ ነው።

ከሐሙሱ የኦሮሚያ ፖሊስ መግለጫ መረዳት እንደተቻለው፤ እኩይ ተግባር ሊፈጸምባቸው የነበሩ የተባሉ የጦር መሣሪያዎች የተያዘ ሲሆን፣ ፖሊስ ባደረገው ክትትል 14 ክላሽ 26 የእጅ ቦንብና 103 ሽጉጦችን መያዙ ነው።

መግለጫውን የሰጡት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አክለው እንዳመለከቱትም፤ በዓሉ በሰላም እንዳይከበር ከኦነግ ሸኔና ከሕወሓት ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ አካላትን ሕብረተሰቡ ጥቆማ እንዲያደርግም ጥሪ አስተላልፈዋል። ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ የኢሬቻ በዓል በአባ ገዳዎች ውሳኔ ከስድስት ሺህ ባልበለጠ ታዳሚዎች የሚከበር ይኾናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ