በትግራይ ክልል ምክር ቤት ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጠበት
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አደም ፋራህ
-
የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጎማ አያደርግም
-
የፌዴራል ተቋማት ከክልሉ ተቋማት መረጃ መለዋወጥ አይችሉም
-
ከቀበሌ፣ ወረዳና ከተማ አስተዳደሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወሰናል
ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፳፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 7, 2020)፦ የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ክልል ምክር ቤትና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በኾነ ምርጫ የተቋቋሙ በመኾኑ፤ ለእነዚህ አካላት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጐማ ማድረግ እንደማይችል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ገለጹ።
አፈ ጉባዔው አቶ አደም ፋራህ ትናንት በትግራይ ክልል ምክር ቤት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ፤ ዛሬ በውሳኔው ዙሪያ በሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ፤ ትናንት በተወሰነው መሠረት ከውሳኔዎቹ መካከል ከክልሉ ምክር ቤት ካቢኔና ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካላት ጋር ግንኙነት የሚቋረጥ በመኾኑ የበጀትም ጉዳይ ከዚሁ ጋር የተያያዘ መኾኑን ማብራሪያቸው አመልክቷል።
እንደ አፈ ጉባዔው ገለጻ የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ መስጠት የሚችለው ለሕጋዊ አካል ብቻ በመኾኑ፤ ሕጋዊ ላልኾነ አካል የበጀት ድጐማ ማድረግ የማይቻል መኾኑን ነው።
“ከዚህ አኳያ የክልሉ ምክር ቤትና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ምርጫን ተከትሎ የተቋቋሙ ስላልኾኑ ሕጋዊ አይደሉም” ያሉት አቶ አደም፤ ስለዚህ የፌዴራል ተቋም ከእነዚህ አካላት ጋር ግንኙነት ማድረግ ስለማይችል፤ ለእነዚህ አካላት የፌዴራል መንግሥት የበጀት ድጐማ ማድረግ እንደማይቻል አስታውቀዋል።
አያይዘውም ከወረዳ፣ ከከተማና ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋር በቀጣይ ስለሚኖረው ግንኙነት በተመለከተ፤ በተለይ ሕዝቡ ማግኘት የሚገባውን መሠረታዊ አገልግሎቶች ማግኘት እንዲችል ጥናቶች ይደረጋል። ይህ በአስፈጻሚው አካል በኩል በጥራት ላይ በመመሥረት ስለሚገባው ግንኙነትና አግባብ ሕዝቡ ማግኘት የሚገባው አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ በቀጣይ በአስፈጻሚው በኩል የሚታይ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ፌዴራል መንግሥት ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ግንኙነት አቋረጠ ሲባል ምን ማለት እንደኾነ ሲገልጹም፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚው ወይም ካቢኔው በሕገ መንግሥቱ ቅቡልነት የላቸውም፤ ሕጋዊ አካላት አይደሉም። ስለኾነም ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና ካቢኔ ጋር ምንም ዐይነት ሕጋዊ ግንኙነት ማድረግ አይችሉም ማለት ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ከዚህ አንጻር ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከትግራይ ክልል ምክር ቤትና ካቢኔ ጋር ወይም በክልል ደረጃ ካሉ አስፈጻሚ አካላትን እንደ ሕጋዊ አካላት በመቁጠር ደብዳቤ መጻጻፍ፣ ዶክመንት መላላክ፣ የፌዴራል ተቋማት ለክልል ተቋማት የሚሰጧቸውን ድጋፎች መስጠት፣ በፌዴራል ደረጃ ላይ በሚካሔዱ መድረኮች ማሳተፍ እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶችንና የመሳሰሉትን መስጠት አይችሉም ማለት እንደኾነ አመልክተዋል።
ይህ ሊወሰን የቻለውም የትግራይ ክልል መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ሕወሓት የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ ባከበረ መልኩ ማስተካከያ ባለማድረጉ መኾኑን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፤ የትግራይ ሕዝብ ኢ-ሕገመንግሥታዊ አካሔድ እየተከተለ ባለ ቡድን ምክንያት ከሰላም ልማትና መሠረታዊ አገልግሎት አንጻር እንዳይጐዳና የትግራይ ሕዝቦች እንደ ሌሎች የትምህርት፣ የጤና፣ የንጹሕ ውኃ አገልግሎት እንዲሁም የምግብ፣ የደኅንነትና የመጠጥ ውኃና የኑሮ ሁኔታ ማሻሻያና ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል ታስቦ ውሳኔው ስለመወሰኑም አስረድተዋል።
“ይሔ ለትግራይ ሕዝብ ካለን ክብር አንጻር ታስቦ የተወሰነ ነው” ያሉት አቶ አደም፤ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌሎች ሕገ መንግሥቱ ያጐናጸፋቸውን መብቶች ሊያገኙና ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጽኑ እምነት ስላለም ነው በማለት አክለው ተናግረዋል።
ይህንን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ በተግባር ለመቀየር ስለሚሠሩ ሥራዎች በተመለከተም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጥናት ላይ ተመሥርቶ የሚሔድበት ይኾናል ብለዋል።
ፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልል ደግሞ ውሳኔው ለሚመለከታቸው አካላት የማሳወቅ፣ በሚመለከታቸው አካላት ውሳኔው ስለመፈጸሙ ክትትል ማድረግ፣ ከውሳኔ አፈጻጸሙ ጋር በተያያዘ ክፍተቶች ከተፈጠሩ በውሳኔው ማዕቀፍ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና ሪፖርት ማድረግን የሚጨምር ሥራ ይሠራል በማለት ማብራሪያቸውን ቋጭተዋል። (ኢዛ)



