Lidetu Ayalew

አቶ ልደቱ አያሌው

ሁለተኛው ክሳቸው በፍርድ ቤት በመጪው ዓርብ ይነበባል

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 12, 2020)፦ አቶ ልደቱ አያሌው ሕገ መንግሥቱን ለመናድ በማሰብ የተለያዩ ሕገ መንግሥት የሚቃረኑ የሽግግር ሰነዶችን በማዘጋጀት በሚል በተከሰሱበት ሁለተኛው ክስ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተገለጸ።

አቶ ልደቱ በተከሰሱበት ሁለተኛው ክስ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት፤ የተከሰሱበትን ወንጀል በችሎት ለማንበብ ነበር።

ኾኖም አቶ ልደቱ ዛሬ ጠበቆቼ ባለመገኘታቸው፤ ጠበቆቼ ባሉበት ተማክሬ ይነበብልኝ በማለታቸው ክሱ ሳይነበብ ቀርቷል። በዚሁ መሠረት ክሱን በችሎች በንባብ ለማሰማት ፍርድ ቤቱ የፊታችን ዓርብ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል።

ሁለተኛው የክስ መዝገባቸው በ381 ገጽ የቀረበ ስለመኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ የክሱ ዋነኛ ጭብጥ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 238 ንዑስ አንቀጽ አንድና 256 በመተላለፍ ሕገ መንግሥቱን ለመናድ በማሰብ የሚል ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ሕገ መንግሥቱን የሚቃረኑ የሽግግር ሰነዶችን በማዘጋጀት ወንጀል የሚልም የያዘ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዚህ ክስ ቀደም ብሎ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘት ወንጀል የተከሰሱበትን ጉዳይ ለመመልከት፤ ነገ ማክሰኞ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ የተያዘ መኾኑ ይታወቃል። በዚህም መሠረት በሁለቱ ክሶች በዚህ ሳምንት ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

በምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቶ ልደቱን እንዲለቅ የተሰጠውን ትእዛዝ እንዲፈጽም የሚያመለክተውን ደብዳቤ ፖሊስ በእንቢተኝነት አለመቀበሉን የኢዴፓ ሊቀመንበር ዛሬ በመረጃ ገጻቸው ጠቅሰዋል።

ነገ ፍርድ ቤቱ የቀጠረው ፖሊስ አቶ ልደቱን ካልለቀቀ፤ ያለቀቀበትን ምክንያት መልስ እንዲሰጥና የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ለማሰማት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ