የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትግራይ ክልል ተወካዮች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
የደምወዝ እገዳና የተሰጣቸውን የመኖሪያ ቤት መቀማት ከእርምጃዎቹ ውስጥ ሊኾኑ እንደሚችሉ ተገምቷል
ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 21, 2020)፦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በማይገኙ የትግራይ ክልል ተወካዮች (የምክር ቤት አባላት) አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አስታወቁ።
አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ይህንን ያስታወቁት ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ ሲሆን፤ በዚህ መግለጫቸው የትግራይ ክልልን በመወከል የምክር ቤቱ አባላት በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ላይ የማይገኙ ከኾነ እርምጃ የሚወሰድባቸው መኾኑን አመልክተዋል።
ምክር ቤቱ ባካሔዳቸው ሁለት ስብሰባዎች ላይ ከአንድ የትግራይ ክልል ተወካይ በስተቀር ሌሎቹ የክልሉ ተወካይ የምክር ቤት አባላት አለመገኘታቸውን ያስታወሱት አፈ ጉባዔው፤ ተወካዮቹ በስብሰባዎቹ እንዲገኙ ጥረቶች እየተደረጉ እንደኾነም ገልጸዋል።
የምክር ቤቱን ጥሪ ተቀብለው የማይገኙና በስብሰባዎቹ ላይ ሳይሳተፉ የሚቀሩ ከኾነ፤ ምክር ቤቱ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቀዋል።
ምክር ቤቱ የአስተዳደራዊ እርምጃ ምን ሊኾን እንደሚችል ባይጠቀስም፤ ማንኛውም ችግር በውይይት፣ በሕግና አመራር መፍታት እንጂ አገርን የማፍረስና ሕግን የመተላለፍ ተግባር መፈጸም የለበትም በማለት አፈ ጉባዔው በዚሁ መግለጫ ላይ ጠቅሰዋል።
እነዚህ የትግራይ ክልል ተወካዮች በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያልተገኙበትን ምክንያት ባያሳውቁም፤ ሕወሓት የክልሉ ተወካዮች በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ እንዳይገኙ ካስተላለፈው መልእክት ጋር የተገናኘ እንደኾነ ይታመናል።
አንዳንድ መረጃዎች ለእዚህ አባላት ጥሪ ያደረገው ሕወሓት ከምክር ቤቱ አባልነት ለቀው ወደ ትግራይ ክልል ከመጡ ለዚህ ተግባራቸው ቤት መገንቢያ ቦታ ይሰጣችኋል መባላቸውን ነው።
የክልሉ ተወካዮች በምክር ቤቱ ስብሰባዎች ባለመገኘታቸው ይወሰዳሉ ተብሎ ከሚጠበቁ እርምጃዎች መካከል፤ በአባልነታቸው ያገኙ የነበረውን ደመወዝ ማቋረጥ፣ እንዲሁም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው የተሰጣቸውን መኖሪያ ቤት ለቀው እንዲወጡ ጭምር እንደሚኾን ይታመናል። (ኢዛ)



