ነፃ በወጡ የትግራይ አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳደር እንደሚቋቋም ተገለጸ
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ
ሕወሓት በአምስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሠራጨ ነው
ኢዛ (ረቡዕ ኅዳር ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 11, 2020)፦ ከጥፋት ኃይሉ ነፃ በወጡ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ጊዜያዊ አስተዳደር የሚቋቋምለቸው መኾኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነአ ያደታ ዛሬ ረቡዕ ኅዳር 2 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ አስታወቁ። ቡድኑ በአምስት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ሐሰተኛ መረጃዎችን እያሠራጨ መኾኑንም ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ከጽንፈኛው ሕወሓት ቡድን ነፃ የወጡ የትግራይ አካባቢዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅና የማደራጀት ሥራ ይሠራል ብለዋል።
ለአካባቢው ነዋሪዎች ሥልጠናዎችን በመስጠት በማደራጀትና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ማከናወን እንዲጀምሩ የሚደረግ መኾኑንም በዛሬው መግለጫቸው አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትግራይ እየተከናወነ ያለውን የሕግ የማስከበር እርምጃ ከትግራይ ሕዝብ ጋር እየተደረገ ያለ ጦርነት የማስመሰል አዝማሚያ መኖሩን የጠቀሱት ሚኒስትሩ የአጎራባች ክልሎች ግዛት ማስፋፋት ማስመሰል፣ ጽንፈኛው ኃይል የፈጸመውን ክህደት ተራ ወንጀል አስመስሎ ማቅረብ፣ ሠራዊቱ በንጹኀን ዜጎችና በመሠረተ ልማት ላይ ጥቃት እየፈጸመ ነው በሚል የሐሰት መረጃ እያሠራጩም ነው ብለዋል።
ሕብረተሰቡ መረጃዎቹ ከእውነት የራቁ መኾናቸውን ሕዝቡ መረዳት እንዳለበት አስገንዝበው፤ የሐሰት ወሬዎችን የሚያሠራጩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።
ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን ሐሰተኛ መረጃ በመፍጠር ወደ ማወናበድ መግባቱ የማሴርና የማደናገር ተፈጥሯዊ ባሕርይ እንደኾነ ያመለከቱት ዶክተር ቀንአ፤ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ የሚገኘው መከላከያ ሠራዊቱ በአጭር ጉዜ ውስጥ ወንጀለኛ ቡድኑን በቁጥጥር ሥር አውሎ ለሕግ እንደሚያቀርብ አረጋግጣለሁ ብለዋል።
“በትግራይ ክልል ከጽንፈኛው ኃይል ነፃ የወጡ አካባቢዎች እንዲሁም እጅ የሚሰጡ ታጣቂዎች ጉዳይ በብሔራዊ ደረጃ በተቋቋመ ኮሚቴ እየተመራ ነው” በማለትም አስረድተዋል። (ኢዛ)



