ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረጉ በረራዎች ተሰረዙ
ጎንደር ዐፄ ቴዎድሮስ ኤርፖርት
ምክንያቱ በባሕር ዳር እና በጎንደር የተከሰተውን የሮኬት ጥቃት ነው
ኢዛ (ቅዳሜ ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 14, 2020)፦ በባሕር ዳር እና በጎንደር የተከሰቱትን ፍንዳታዎች ተከትሎ ጥቃቱ በደረሰ ማግስት ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ይደረጉ የነበሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች እንዲሰረዙ ተደርገዋል። የሮኬት ጥቃቱ የፈጸመው የሕወሓት ጁንታ ቡድን ትናንት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ላይ ነበር።
በአደጋው ማግስት ዛሬ ቅዳሜ ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ላሊበላ ከተሞች የተያዙ በረራዎች በሙሉ ላልተወሰን ጊዜ እንዲቋረጡ በመደረጉ፤ ወደ እነዚህ ከተሞች በረራ የነበራቸው ተጓዦች ከበረራቸው ተስተጓጉለዋል።
እነዚህ በረራዎች መሰረዛቸውንም አየር መንገዱ ያስታወቀ ሲሆን፤ በዕለቱ በረራ ለነበራቸው ተጓዦች ይህንኑ ለማስታወቅ ተገድዷል። (ኢዛ)



