በጥፋት ተልዕኮ የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦች ድሬ ዳዋ ላይ ተያዙ
የድሬ ዳዋ ከተማ
ከጁንታው የሕወሓት ቡድን ጋር ግንኙነት አላቸው
ኢዛ (ቅዳሜ ኅዳር ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 14, 2020)፦ የድሬ ዳዋ ፖሊስ በድሬ ዳዋ የጥፋት ተልዕኮ እንዳላቸው የተጠረጠሩ 18 ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታወቀ። ግለሰቦቹ ከሕወሓት ጁንታ ቡድን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው አክሎ ገልጿል።
በሕዝብ ጥቆማ በተለየዩ ቀናት የተያዙት 18 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው መኮኑንም የከተማው ፖሊስ ገልጿል።
በእነዚህ ተጠርጣሪዎች ላይ ዘጠን ሽጉጦች፣ ጥይቶች፣ የተለያዩ አገሮች ፓስፖስቶችና ሰነዶች መገኘታቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የከተማዋ ፖሊስ ኮምሽነር ዓለሙ መግራ፤ “የጥፋት ቡድኑን ለመደገፍ በለገሀሬ እና ጀርባ በሚባሉ ሰርፈሮች ኹከትና ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል” ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ የከተማዋን ጸጥታ ለመጠበቅ ምክር ቤት ተዋቅሮ ከተለያዩ የጸጥታ ተቋማት ጋር የጥበቃ ቁጥጥር እየተደረገ መኾኑን የኮምሽነሩ መግለጫ ያመለክታል። (ኢዛ)



