በጽንፈኛው ቡድን ላይ የሚወሰደውን እርምጃ ዓለም ሊደግፈው እንደሚገባ ተገለጸ
አቶ ጌታቸው ረዳ - የሕወሓት ጁንታ ቡድን ነባር አባልና ቃል አቀባይ
“ጁንታው ቡድን የፈጸማቸውን ወንጀሎች አቶ ጌታቸው ረዳ አምነዋል”
ኢዛ (እሁድ ኅዳር ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 15, 2020)፦ ጽንፈኛውን የሕወሕት ቡድን ለሕግ ለማቅረብ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ሊደግፈው እንደሚገባና ጽንፈኛው ቡድን በንጹኀን ላይ እያደረሰ ያለውን የግፍ ተግባር ሊያወግዙት እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የጁንታው ቡድን ጥቃት ማድረሱን በቡድኑ ቃል አቀባይ የተነገረውን በመጥቀስ በመግለጫው ያስታወቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት፤ ሕገወጡ ቡድን የፈጸመውን ወንጀሎች እያወጡም ነው ብሏል።
“የጁንታው ቡድን፤ በቡድኑ ተፈጸሙ ያላቸውን አንዳንድ ተግባራት በዚሁ መግለጫ ያተተ ሲሆን፤ መንግሥት በቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ ሊደግፍ ይገባል” ብሏል ዛሬ እሁድ ኅዳር 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የወጣው መግለጫ።
የሕወሓት ጁንታ ቡድን ነባር አባልና ቃል አቀባይ (አቶ ጌታቸው ረዳ) ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ ጁንታው ቡድን የሰሜን ዕዝ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱንና የተፈጸመውን ወንጀል ማመናቸውን ያወሳው የጠ/ሚ ጽ/ቤት መግለጫ፤ መንግሥትም ሕገወጥ ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ ያለው አቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ የጠነከረ መኾኑን ገልጿል። (ኢዛ)



