PM Abiy Ahmed (L) and Dr. Debretsion Gebremichael (R)

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

ከሚያዝያ 2010 እስከ ኅዳር 2013 ዋና ዋና ጉዳዮች ይዟል

ኢዛ (ሰኞ ኅዳር ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 23, 2020)፦ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኾነው ከተሰየሙበት ዕለት ጀምሮ የሕወሓት ቡድንን በትክክለኛ አቅጣጫ እንዲጓዝና ልዩነቶች ሲፈጠሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሲያደርጉ የነበረውን ጥረት የሚያመለክት መረጃ ይፋ ኾነ።

“የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የጽንፈኛው ሕወሓት ምላሽ” በሚል ርዕስ የተሰናዳው ይህ መረጃ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያዝያ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ኅዳር 2013 ዓ.ም. ድረስ ለሕወሓት ያቀረቡትን ጥሪና ሕወሓትን ለመመለስ ካደረጉዋቸው ጥረቶች ዋና ዋና የሚባሉት የተጠቀሱበት ነው።

የሕወሓት ቡድን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡለትን ጥሪዎች ሳይቀበል፤ በአንጻሩ ሲፈጽማቸው የነበሩ ተግባራትንም በተወሰነ ደረጃ የሚያመለክት ነው።

ዛሬ ማምሻውን በብልጽግና ፓርቲ የመረጃ ገጽ የተለቀቀው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረቶችና የሕወሓትን ምላሽ የሚያመለክተው መረጃ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪና የጽንፈኛው ሕወሓት ምላሽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወርሃ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ላይ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ለትግራይ እንደ ሁልጊዜው በማክበርና በሰላምና ልማት ላይ እንዲያተኩር ጥሪ በማቅረብ ሕወሓትም እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በሰላምና አገራዊ ፖለቲካ ዙሪያ በጋራ እንዲሠራ ተደጋጋሚ ጥቂ አቅርበዋል።

ፓርቲና ሕዝብ የተለየ መኾኑን ሁሉም እንዲገነዘብ ሲመክሩና ሲያስረዱ ቆይተዋል፤

ከዚህ አኳያ ለሕወሓት በተደጋጋሚ በሰላማዊ መልኩ እንዲንቀሳቀስና ለውጡን ለትግራይ ሕዝብ ሰላም እንዲጠቀምበት ተደጋጋሚ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ በታች ዋና ዋናዎቹ እንደ አብነት ቀርበዋል።

ሚያዝያ 5 ቀን 20 10 ዓ.ም.

• ወደ መቀሌ በማምራት ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት አደረጉ፤

የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መንግሥታቸው ከክልሉ አመራር ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ ገልጸው፤ የትግራይ ሕዝብም በሰላም እና ልማት ላይ እንዲያተኩር፣ ክልሉን የሚመራው ሕወሓትም በሕዝቡ የፀረ ድህነት ትግል ላይ አትኩሮ እንዲሠራ ጥሪ አቀረቡ። የክልሉ ነዋሪዎችም ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ፤ እንዲሁም ለውጡን ተከትሎም ሥጋት አድሮባቸው የነበሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን አበረታትተውና ጥያቄያቸውን ተቀብለው ተመለሱ።

ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም.

• ወደ አክሱም በማቅናት በአካባቢው ከሚገኙ ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ፣

በአደጋ ላይ ያሉትን የአክሱም ሐወልቶች የጎበኙ ሲሆን፤ ሐውልቶቹ በሚጠበቁበት ሒደት ላይ ከጣልያን መንግሥት ጋር ንግግር እያደረጉ መኾኑን ተናገሩ። ሕዝቡ ሰላም፣ ፍቅር፣ ይቅርታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየታዩ ያሉ ፖለቲካዊ የጸጥታ ችግሮች እንዲፈቱ፣ ክልሉን የሚመራው ሕወሓትም ለሰላም በጋራ እንዲሠራ ጥሪ አቀረቡ።

የካቲት 04 ቀን 2011 ዓ.ም.

• ማናቸውንም ዐይነት ችግሮች በአገር በቀል መፍትሔ እንዲፈቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን በማቋቋም ጥሪ አቀረቡ፤

በትግራይ ክልል መንግሥትና አጎራባች አካባቢዎች የሚታዩ አለመግባባቶች በአገር ውስጥ ከተለያዩ ወገኖች በተውጣጡ ታዋቂ ሰዎች የጋራ ሽምግልና ጥረት እንዲፈቱ በሕዝብ የተመረጡ ገለልተኛ የአገር ሽማግሌዎች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ ኮሚሽን እንዲቋቋም አደረጉ።

ለዚህም ሁሉም ወገን፣ በተለይም የትግራይ መንግሥት እንዲተባበር ጥሪ አደረጉ፤

ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግጭቶች ምክንያት በሕዝቦች መካከል የተደራረቡ የቁርሾ ስሜቶችን ለማከም፤ እውነት እና ፍትሕ ላይ መሠረት ያደረገ እርቅን ለማውረድ እንዲያግዝ የተቋቋመ ነው። በወቅቱም፣ የኮሚሽኑ አባላት ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከመድሎ በጸዳ መልኩ ሥራቸውን በአግባቡ እንደሚወጡ አደራ አስተላለፉ።

መንግሥትም በእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ እንደማይገባ ቃል ገቡ።

በተመሳሳይ በክልሎች መካከል የሚነሳን የማንነትና ወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሰላም የሚፈታ የወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚቴ አዋቀሩ፤

ነገር ግን ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን በዚህ ወቅት ሒደቱን አጣጥሎ፤ እንደማይቀበልም በይፋ አሳውቆ ነበር።

ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.

• 50 አባላትን ያካተተ የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የአገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ተላከ፣

በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና ትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለው መልካም ያልኾነ ግንኙነት በንግግር እንዲፈታ አንድ የሽማግሌዎች ቡድን ወደ መቀሌ ላኩ፤

ቡድኑ በመቀሌ ከትግራይ ክልል መንግሥትና የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ቢወያይም፤ የወቅቱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለቡድኑ ይሁንታ ነፈጉት፤ ይልቁንም ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ በወቅቱ አስካሁን ድረስ የት ነበራችሁ፤ የሚያስፈልገው እርቀ ሰላም አይደለም በሚል በሽማግሌዎች ጥረት ላይ ውኃ ቸለሱ፤ የቡድኑ አባላትም በሕወሓት ጀሌዎች ስድብና ማዋረድ ደረሰባቸው፤

ጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም.

• ሕወሓትና ጥቂት ደጋፊዎቹ ለውጡን እንደ እድል በመጠቀም በጋራ እንዲሠሩ፣ ካልተገባና አገር አፍራሽ የፖለቲካ ትርፍ ጉዞ እንዲታቀቡ በምክር ቤት ቆይታቸው መከሩ፤

ለሕዝብ ተወካዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ “የኢሕአዴግ”ን ወሕደት አሃዳዊ መንግሥት ለመመስረት የሚደረግ ሩጫ ነው እያሉ ሕዝብን የሚያደናግሩ አካላት እንዳሉ ጠቅሰው፤ ኢሕአዴግ ፓርቲ እንጂ አገረ መንግሥት እንዳልኾነ አስረዱ።

ዜጎችም ኾነ ብለው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እኩይ ተግባር ውስጥ በገቡ አካላት እንዳይደናገሩ መከሩ።

ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም.

• መንግሥት በዜጎች ሕይወት ላይ በመቆመር ጥቅማቸውን ለማስመለስ የሚሠሩትን እንደማይታገስ አሳሰቡ፣

በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረ ረብሻ የ86 ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን አስመልክተው ባስተላላፉት መልእክት፤ በፖለቲካ ፓርቲ ስም ተሸፍነው ያጡትን ጥቅም ለማስመለስ ኢትዮጵያውንን በብሔር ከፋፍሎ ለማጫረስ በስውር የሚሠሩ ቡድኖች ግለሰቦች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳሰቡ።

የመንግሥትን ሆደ ሰፊነት እንደ ፍርሃት በመቁጠር ሕግን በሚጥሱ አካላት ላይ መንግሥት እንደማይታገስ አጽንኦት ሰጥተው ገለጹ።

ሚያዝያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም.

• የትግራይ መንግሥት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን በማክበር የትግራይን ሕዝብ ከኮሮና በመጠበቅ ሕግ እንዲያከብር አሳሰቡ፤

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አገራዊው ምርጫ ማራዘምን ተከትሎ ሕወሓት ውሳኔውን እንደማይቀበለው መግለጹን ተከትሎ ባስተላላፉት መልእክት፤ የትግራይ መንግሥት የምክር ቤቶችን ውሳኔ እንዲያከብርና ኮሮና በተስፋፋበት ወቅት የጨረባ ምርጫ ማካሔዱ ዞሮዞሮ ጉዳቱ የሕዝብ መኾኑን ተገንዝቦ ለሕግ ተገዢ እንዲኾን አሳሰቡ።

ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.

• ሕወሓት አንድ ፓርቲ እንጂ ሕዝብ አለመኾኑን፣ በሕዝቡም ሊነገድበት እንደማይገባ፣ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታወቁ፤

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የኾኑ የሕወሓት ተወካዮች መንግሥት ትግራይን ያገለለ ሥራ እያከናወነ አስመስለው ቅሬታ ባቀረቡበት ወቅት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ የትግራይ ክልል የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ከፍ እንዳለና ለዓመታት ሲጓተት የነበረው የመቀሌ ውኃ ፕሮጀክት እንዲያልቅ መንግሥት ከፍተኛ ብር መድቦ እየሠራ መኾኑን ይፋ አደረጉ፤ “የትግራይ ሕዝብ ሕዝባችን ነው፤ ሕወሓት አንድ ፓርቲ እንጂ ሰላም ወዳዱን ትግራይን ሕዝብ አይወክልም” ሲሉ በተደጋጋሚ የሕዝብ ተወካዮች አባላት ፊት ተናገሩ።

ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.

• ያለችን አንድ አገር ነች፤ ልዩነቶችን በሰከነ አግባብና በሠለጠነ ውይይት እንፍታ ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፤

ወቅታዊ ጉዳይን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለችን አንድ አገር መኾኗን ተረድተው ልዩነቶችን በሰከነ አግባብና በሠለጠነ ውይይት እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም.

• አንድ እግራቸውን የትጥቅ ትግል ሌላኛ እግራቸውን ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ አድርገው ሕዝብን የሚያደናግሩ አካላት እንዲጠነቀቁ አሳሰቡ፤

ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት አንድ እግራቸውን የትጥቅ ትግል ሌላኛ እግራቸውን ደግሞ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ አድርገው ሕዝብን የሚያደናግሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ አሳስበዋል።

የ2013 አዲስ ዓመት ዋዜማ፣

• ሕወሓት መንግሥት የኃይል አማራጮችን እንዲወስድ ከሚያነሳሱ ትንኮሳዎች እንዲታቀብ አሳሰቡ፤

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ ጦርነት ሳይኾን ልማትና ብልጽግና እንደሚያስፈልገው በይፋ ተናግረዋል።

መንግሥታቸውም የትግራይን ሕዝብ ከመርዳት ባለፈ ምንም ዐይነት የግጭት ፍላጎት እንደሌለውም ገልጸዋል። ነገር ግን መንግሥት የተለያዩ የኃይል አማራጮችን እንዲወስድ ሕወሓት ትንኮሳ እያደረገ መኾኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር በትግርኛ ቋንቋ የትግራይ ሕዝብን በስሙ እየነገዱ ወደ ግጭት ሊወስዱት እየሠሩ ያሉ አካላት እንዳሉና ሕዝቡም ይህን አጥብቆ እንዲታገል በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

ሆኖም፤

➢ በእነዚህ ሁሉ ሒደቶች የሕወሓት ጽንፈኛ ቡድን በክልሉ ያሉ የመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ለሥራ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ሕፃናትን ጎዳና ላይ እያስተኙ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋል።

➢ የሠራዊቱ አባላት የዕለት ተዐለት እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ያልተፈለገ ፍተሻ በማድረግም ከፍተኛ እንግልት ሲያደርጉ ቆይታዋል።

➢ የመከላከያ ሠራዊቱ ይህን ሁሉ ትንኮሳ በትዕግሥት ሲያልፍ ቆይቷል።

➢ ይህ አልበቃ ብሎ የአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አዛዥን በመቀሌ አሉላ አባ ነጋ አውሮፕላን ማረፊያ በማገት ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ አድርገዋል።

ጥቅምት 23 ቀን 20 13 ዓ.ም.

➢ የሕወሓት ጁንታ ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ የጽንፈኛው ቡድን መሪ የኾኑት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ጦርነት ትግራይ ላይ እንደማይቀርና ሕዝቡ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅረቡ። ወደ ትግራይ የሚመጡ ማናቸውንም አካላት “እንቀብራቸዋለን” ሲሉ የጦር አውርድ ነጋሪት በአደባበይ ጎሰሙ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.

➢ ጽንፈኛ ቡድኑ ያደራጃቸው የልዩ ኃይሉ ታጣቂዎች በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ አባላት ላይ ከወገን የማይጠበቅ ዘግናኝ ጥቃት በሌሊት ፈጸሙ።

➢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ጽንፈኛ ቡድኑ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም ቀይ መስመር እስኪጥስ ድረስ ሐሳባቸው አንድ ነበር “ሰላም፣ ይቅርታ፣ እርቅና ብልጽግና"። ይህን ሐሳባቸውንም በአገኙበት አጋጣሚ ይፋ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

➢ ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን በሰሜን ዕዝ አባላት ላይ አሳፋሪ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ (በነገራችን ላይ ጽንፈኛ ቡድኑ ጥቃት መፈጸሙን የቡድኑ አፈቀላጤ ሴኮ ቱሬ ጌታቸው ማመናቸው ይታወሳል)፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባስተላለፉት መልእክት መንግሥት ለሰላም ሲል በሆደ ሰፊነት በርካታ ትንኮሳዎችን ማለፉን ጠቁመዋል። መንግሥት ይህን ያደረገውም “የትግራይ እናቶች እስከ መቼ ያለቅሳሉ” በሚል መርኅ መኾኑንም ነው ያስረዱት።

ጥቅምት 25/2013 ዓ.ም.

• ቀዩ መስመር ስለታለፈ፣ የሰላም ጥሪው ዋጋ ማጣቱን በመግለፅ ሕግ የማስከበር እርምጃ ግድ መኾኑን አሳወቁ፤

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ንጋት 11 ላይ በሠራዊታችን ላይ በሕወሓት ጁንታ ያልተጠበቀና ዘግናኝ ጥቃት መፈጸሙን በኀዘን አስታወቁ፤ ቀይ መስመር የታለፈ መኾኑን፣

ለረጅም ጊዜ ለሕወሓት ቡድን የሰላም ጥሪ ሲደረግ ቢቆይም፤ ይህን ባለመቀበልና የእናት ጡሽ ነካሽ በመኾን የማይደፈረውን የሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት አስጠባቂ የኾነው ኃይላችን ተደፈረ ሲሉ ገለጹ፤

መንግሥት በዚህ አረመኔ ቡድን ላይ እርምጃ እንዲወስድም ጥብቅ ትእዛዝ አስተላለፉ፤ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ግን የማይለወጥ አቋም እንዳለውና የትግራይ ሕዝብንና የሕወሓት ጁንታን መላው ሕዝብ ለያይቶ እንዲመለከትም ለመላው ሕዝብ አሳሰቡ፤

ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም.

ባስተላለፉት መልእክት በሕግ ማስከበር እርምጃውን ተከትሎ የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ የትግራይ ልዩ ኃይል አባላትና ሚኒሻዎች በሦስት ቀናት ውስጥ እጃቸውን እንዲሰጡም ጊዜ ገደብ ሰጥተዋል፤ በርካታ ሰላም ወዳድ የክልሉ ጽጥታ አካላትም እድሉን ተጠቅመዋል።

አሻፈረኝ ብለው በቀሩት ላይ በሚወሰደው የሕግ ማስከበር እርመጃ ወቅት ንጹኀን ዜጎች እንዳይጎዱም የመከላከያ ሠራዊቱ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ኦፕሬሽኑን እንዲያከናውንም ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

በተቃራኒው ጽንፈኛው የሕወሓት ጁንታ በአማራ ክልል ርዕሰ መዲና ባሕር ዳር፤ እንዲሁም በጎንደር ከተማ ንጹኀን ላይ ትኩረት ባደረገ መልኩ ሮኬቶችን ተኩሷል፤ በመሠረት ለማት ላይም ጉዳት አድርሷል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!