Addis Ababa

በአዲስ አበባ የሕገወጥ የመሬት ወረራው ከተካሔደባቸው አካባቢዎች አንዱ (ፎቶ፣ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘጋቢ ላይ የተወሰደ ስክሪንሾት)

የተሰረቀው መሬት ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ኾኗል
በሕገወጥ መንገድ በተመሠረቱ 64 መንደሮች 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ተይዟል

ኢዛ (ረቡዕ ታኅሣሥ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. December 16, 2020)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ የተወረረውን መሬት ከሥር ከሥር በሚደረግ ማጣራት እየተገኘ ያለው መረጃ የከፋ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ እየተመላከተ ሲሆን፤ ዛሬ ይፋ በተደረገው መረጃም በሕገወጥ መንገድ የተያዘው መሬት ከ13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ደርሷል።

የሕገወጥ የመሬት ወረራው በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተፈጸመ ሲሆን፤ ከ13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት በሕገወጥ መንገድ ተወረው የተገኙት በ121 ወረዳዎች ነው ተብሏል።

ከዚህ ቀደም በተወሰኑ ወረዳዎች የተደረጉት ማጣራቶች የተወረረው መሬት አነስተኛ ቁጥር የሚያሳዩ ቢኾንም፤ ሰሞኑን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘጋቢ መረጃ ይፋ እንደተደረገው፤ እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረት በከተማዋ 13,523,634 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በሕገወጥ መንገድ የተያዘ መሬት መገኘቱን የከተማዋን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጠቅሶ ወቅታዊውን መረጃ ይፋ አድርጓል።

ከለውጡ ወዲህ ቀዝቀዝ ብሎ የነበረው የመሬት ወረራ፤ እንደአዲስ አገርሽቶ እየተስፋፋ ስለመኾኑ የሚያመለክተው ይኸው መረጃ፤ ሕገወጥ ተግባሩ በስፋት የታየባቸው ብሎ የጠቀሳቸው ቦሌ፣ የካ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ እና ጉለሌ ክፍለ ከተሞችን ነው።

በሕገወጥ የመሬት ወረራው የሪል ስቴት አልሚዎችና የሃይማኖት ተቋማትም ተሳታፊ መኾናቸው የታወቀ ሲሆን፤ በሪል ስቴት አልሚዎች 184 ሺህ 208 ካሬ ሜትር በሕገወጥ መንገድ ተይዞ መገኘቱ ታውቋል። የሃይማኖት ተቋማትም እስካሁን ባለው መረጃ በሕገወጥ መንገድ የያዙት የመሬት መጠን ደግሞ ከ97 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ ይኾናል ተብሏል።

በአኀዝ የተደገፈው የሕገወጥ የመሬት ወረራ ማሳያ ተብሎ የተጠቀሰው ሌላው ማሳያ፤ በሕገወጥ መንገድ በተመሠረቱ 64 መንደሮች ውስጥ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ካሬ ሜትር መሬት የተወረረ ሲሆን፤ አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር ባዶ መሬትም በሕገወጥ መንገድ ታጥሮ መገኘቱ ይፋ ኾኗል።

ምክትል ከንቲባዋ ይህ ሥር የሰደደ ድርጊት የከረመ መኾኑን ጠቅሰው፤ የመሬት ወረራው ላይ ተሳታፊ የኾኑ አካላት ብዙ ቢኾኑም፤ በዋናነት ግን የችግሩ ዋነኛ ተዋንያን ከመንግሥት ተቋማት ዘንድ ስለመኾኑ መግለጻቸውም ተጠቅሷል።

በዚህን ያህል ደረጃ እየተገለጸ ያለው የከተማዋ የመሬት ወረራ፤ በቀጣይ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለው ጥያቄ ደግሞ አሳሳቢ ኾኖ መጥቷል።

ሥር የሰደደው ችግር ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፤ በከተማዋ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ተጽእኖ ቀላል ላይኾን ይችላል የሚለው አመለካከት በብዙዎች ዘንድ እየተነሳ ነው። ከዚህ ቀደም “የጉድ ከተማ” በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ከመሬት ወረራ፣ ባለቤት ስለሌላቸው ሕንጻዎችና ሕገወጥ ተግባራትን የሚያሳይ ሪፖርታዥ በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ማስነበባችን አይዘነጋም(ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ