የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔውን አሳደገ
የኢትዮጵያን ንግድ ባንክ
በሁሉም አገልግሎቶቹ ላይ ዋጋ ጭማሪ አድርጓል
ለቤቶች የሚሰጥ ብድር ወለድ ወደ 10.5 በመቶ ከፍ ብሏል
ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 13, 2021)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የብድር ወለድ ምጣኔውን ጨምሮ በሁሉም አገልግሎቶች ክፍያ ላይ የዋጋ ጭማሪ አደረገ።
በኢትዮጵያ ትልቁ ባንክ በመኾንና ወደ 80 ዓመታት ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤ የወለድ እና የአገልግሎት ክፍያውን የጨመረው የባንኩ ገቢና ወጪ ባለመጣጣሙ ነው።
የብዙ አገልግሎቶቹ ክፍያ በነፃ እና እጅግ ባነሰ ዋጋ ሲሠራ የቆየ መኾኑን ባንኩ ያስታወቀ ሲሆን፤ በዚህ መልክ እየሰጠ ያለው አገልግሎት የባንኩን ሕልውና በመፈታተን ላይ በመኾኑ፤ አዲስ የአገልግሎት ተመን እንዲያወጣ አስገድዶታል። አዲስ ተሻሽሎ አገልግሎት ላይ የሚውለውን የአገልግሎት ታሪፍ አስመልክቶ ባንኩ እንዳስታወቀው፤ ለቤቶች ልማት በ9.5 በመቶ የወለድ ምጣኔ ያቀርብ የነበረውን ብድር ወደ 10.5 በመቶ አሳድጓል።
ኮርፖሬት ለሚባለውና ለትልቅ ብድሮች ይጠየቅ የነበረውን የስምንት በመቶ ወለድ ወደ ዘጠኝ በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን አስታውቋል።
ባንኩ ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍያ ማሻሻያ ካደረገባቸው ውስጥ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር በተያያዙ አገልግሎቶች ላይ ሲሆን፤ በተለይ ለዘጠና ቀናት ለሚመለስ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት እስካሁን ይከፈለበት የነበረው የ5.5 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ ወደ 9.5 በመቶ ከፍ ብሏል።
መሠረታዊ ለሚባሉና መንግሥት ለሚያስገባቸው የተወሰኑ ምርቶች ለሚጠየቅ የውጭ ምንዛሪ የሚከፈለው የአገልግሎት ዋጋ ዝቅ ማድረጉን ለማወቅ ተችሏል።
በባንኩ መረጃ መሠረት በሁሉም አገልግሎቶች ላይ ጭማሪ ያደረገ ሲሆን፣ የአብዛኛዎቹ አገልግሎቶች የክፍያ ምጣኔ ጭማሪ ከአንድ በመቶ በታች ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ1800 በላይ ቅርንጫፎችን ይዞ በመላ አገሪቱ የሚንቀሳቀስ ባንክ ሲሆን፤ በ2012 በጀት ዓመት ወደ 14 ቢሊዮን ብር አትርፎ ነበር። ይህ ትርፍ ግን በ2011 በጀት ዓመት አግኝቶ ከነበረው 17 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ ዝቅ ያለ ኾኖ ተገኝቷል።
በ2013 በግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም በ2012 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደኾነ እየተነገረ ነው። (ኢዛ)



