Kejela Merdasa (OLF)

አቶ ቀጄላ መርዳሳ (የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ)

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው የመሳተፋችን ነገር 50 በመቶ ነው ይላሉ

ኢዛ (ሰኞ የካቲት ፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 15, 2021)፦ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አመራር አባላት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተለያዩ ማጣራቶች ሲያደርጉ መቆየቱ የሚታወስ ቢኾንም፤ ግንባሩ በቀጣዩ ምርጫ (ምርጫ 2013) የመሳተፍ እድል 50 በመቶ መኾኑን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ገለጹ።

የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ቀጄላ መርዳሳ በምርጫው ላንሳተፍ እንችላለን የሚል ግምት ያሳደረባቸው፤ በኦነግ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን መከፋፈል ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አባላቱ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ በወሰነው መሠረት ጉባዔው መካሔድ ባለመቻሉ ነው። በኦነግ ውስጥ ያለውን አለመግባባት በሥራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ፤ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አባላት ይህንን አውቀው ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያከናውኑ የሚለው ውሳኔ ግን በክፍፍል ውስጥ የሚገኘው ኦነግ እስካሁን ጠቅላይ ጉባዔ ማድረግ ያለመቻሉ አጣብቂኝ ውስጥ ከትቶታል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት አቶ ቀጄላ፤ ጠቅላላ ጉባዔው እንዳይደረግ ያደረጉት የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳና ከእርሳቸው ጋር የተሰለፉ የአመራር አካላት ስለመኾናቸው ይጠቅሳሉ። ቦርዱ ስለጉባዔው ለማወያየት የግንባሩን ሊቀመንበር ጨምሮ ሥራ አስፈጻሚ አባላትን ቢሮው ድረስ ጠርቶ የነበረ ሲሆን፤ አቶ ዳውድ ግን ሊገኙ ያለመቻላቸውንም ይጠቅሳሉ።

አቶ ዳውድ በጉዳዩ ላይ ከመነጋገር ይልቅ መራቅ እንደጀመሩና አመራሩን ለመበተን እንደፈለጉ የሚገልጹት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ በቀጣይ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጉዳይ ግን አነጋጋሪ መኾኑ አልቀረም። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ